#eth

#eth


የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ በተጠረጠሩ ግለሰቦች የምርመራ ቡድን ያቀረበውን ይግባኝ ለመወሰን ለመስከረም 21/2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጠ።

በባህር ዳር ከተማ በተፈፀመው የባለስልጣናት የግድያ ወንጀል መረጃ የማሰባሰብና የማጣራት ስራው ባለመጠናቀቁ ክስ መመስረት በሚያስችል ደረጃ ላይ አልደረስኩም ሲል መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው በነብርጋዲየር ጀነራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ የጊዜ ቀጠሮ ይግባኝ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለመስከረም 21/2012 ቀጠሮ ሰጥቷል።

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረውም ቀደም ሲል መርማሪ ቡድኑ በእስር ፍርድ ቤቱና በባህርዳር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበውና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ አስፈላጊ አይደለም ብሎ የዘጋውን መዝገብ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ በማለት ነው።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ለችሎቱ እንዳስረዱትም መርማሪ ቡድኑ የሰው ፣ የሰነድ ፣ የቴክኒክና የፎረንሲክ መረጃ እንዲያሰባስብ በተሰጠው ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ እያሰባሰበ እንደሆነና ዋናውን ክስ ለመመስረት የሚያግዝ የቅድመ ክስ በመመስረት ምስክሮችን ሲያሰማ እንደነበረም ጠቅሰዋል።

ቡድኑ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ከፍርድ ቤቶቹ በተሰጠው ጊዜ አዳዲስ ማስረጃ እያቀረበ ባለመሆኑ መዝገቡን መዝጋታቸውንና ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ማቅረብ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም 44 ቀናት እንደሆኑትና ተጨማሪና አዳጊ ማሳረጃዎችን ማቅረብ እንዳልቻለ አስረድተዋል።

“በዚህም መርማሪ ቡድኑ ግልፅ ቸልተኝነት እያሳየ ነው” ያሉት ጠበቆቹ፤ “በዚህ የተነሳ ደንበኞቻችን ከአላግባብ እየታሰሩ ነው” ብለዋል።

የምርመራ ቡድኑ በበኩሉ ወንጀሉ ውስብስብ ቢሆንም በተሰጠው ጊዜ ጉዳዩን የማጣራት፣ የሰው፣ የሰነድ፣ የፎረንሲክና የቴክኒክ ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ስራ በመሰራቱ ከታሰሩት 270 ተጠርጣሪዎች ጉዳዩን በማጣራት 70 ያህሉ እስኪቀሩ መለቀቃቸው ገልጸዋል።

ነገር ግን የምርመራ ቡድኑ 134 ማስረጃ ያለው ሰነድና 400 ገጽ የፎረንሲክ ምርመራ ማስረጃ ቢቀርብም በፍርድ ቤቱቹ ሰነዱን ሙሉ በሙሉ ሳይመለከቱ የምርመራ መዝገቡን ብቻ በማየት የጊዜ ቀጠሮውን መዝጋታቸውን በቅሬታ አቅርበዋል።

ከጉዳዩ ውስብስብነት አንፃር አሁንም አዳዲስ ማስረጃዎችንና ተጠርጣሪዎችን እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቅሶ፤ አሁንም ቡድኑ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አመልክቷል።

ጉዳዩን ከተፈፀመው ወንጀል ጋር በማያያዝ ከመመርመር ውጭ ሌላ አጀንዳ እንደሌለው የገለጸው የምርመራ ቡድኑ ማንም ሰው ያለጥፋቱ መታሰርና መንገላታት እንደሌለበት በማመንም የማጣራት ስራውን እንደሚቀጥል አቅርቧል።

በመሆኑም ጉዳዩ በጥንቃቄ የሚታይ በመሆኑ አሁንም ተጨማሪ ማስረጃዎች በማስፈለጋቸው ዋናውን ክስ መመስረት በሚያስችል ደረጃ ላይ አለመድረሱን አስታውቋል።

ወንጀሉ በታወቀ፣ ጊዜ፣ በታወቀ ሰውና በታወቀ ሰዓት የተፈፀመና ግልጽ ሆኖ እያለ መርማሪ ቡድኑ ጉዳዩ ውስብስብ ሆኖብኛል የሚለው ተቀባይነት የለውም ሲሉም ተጠርጣሪዎች ቅሬታ አቅርበዋል።

ሁሉንም በጅምላ ይዞ ለማጣራት እያደረገ ያለው አካሄድም ተገቢ ባለመሆኑ በተሰጠው ጊዜ ለይቶ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

የሁለቱን ጉዳይ ያዳመጠው ችሎቱ የቀረበው የሰበር አቤቱታ በመሆኑና አሁን ላይ ደግሞ መደበኛው ፍርድ ቤት ስራ ባለመጀመሩ ጉዳዩን በአፋጣኝ ለማየት ተችሏል።

በመሆኑም መደበኛ ፍርድ ቤቱ ስራ የሚጀምረው መስከረም 20/2011 ዓ.ም በመሆኑ ጉዳዩን በሰበር ሰሚ ችሎት በመደበኛነት ለማየትና የጊዜ ቀጠሮው ይፈቀዳል ወይስ አይፈቀድም የሚለውን መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለመስከረም 21/2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Via #ENA

Report Page