#ETH

#ETH


ከትናንት በስቲያ (ቅዳሜ) ከምሽቱ 1 ሰዓት ገደማ በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ከተማ ሁለት ሰዎች በጥይት ተመትተው መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ይህን መሰሉ ግድያ የዕለት ተዕለት ሰቆቃ ከሆነ ሰነባብቷል።

"ቅዳሜ ምሽት ተኩስ ነበር። በዚያ ተኩስ ሳቢያ ነው ሁለቱ ነዋሪዎች የተገደሉት። እነሱን የገደለው አካል የቱ እንደሆነ ደግሞ መለየት አልቻልንም" በማለት ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል።

ከተገደሉት ሁለቱ ግለሰቦች አንዱ የጊዳሚ ከተማ ቀበሌ 01 ነዋሪ የነበሩት አቶ ነጋሽ ፉፋ ሲሆኑ ሌላኛው ሟች ደግሞ፤ "ከቄለም ገጠራማ ስፍራ የመጡ ናቸው፤ ማንነታቸውን አለየንም" በማለት የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል።

የጊዳሚ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ቱጁባ በበኩላቸው ሟቾቹ አቶ ነጋሽ ፉፋ እና አቶ ያዕቆብ ቶላ እንደሚባሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"አቶ ነጋሽ ፉፋ ቤት አቅራቢያ በቅኝት ሥራ ላይ በነበሩ የልዩ ፖሊስ እና የሃገር መከላከያ አባላት ላይ ቦንብ ተወረወረ፤ ተኩስም ተከፈተ" የሚሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ ቦንምቡን የወረወረው እና ተኩስ የከፈተው አካል አሁን ድረስ እንደማይታወቅ ጠቅሰው፤ ድንገተኛ ጥቃቱ የተሰነዘረው ግን በመንግሥት ኃይሎች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ሟቾቹም "የትኛው አካል በተኮሰው ጥይት እንደተገደሉ'' የታወቀ ነገር የለም ብለዋል አስተዳዳሪው።

"መሸሸጊያ ያጣ ህዝብ"

በምዕራብ ኦሮሚያ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሠራዊት እያለ የሚጠራ አካል በስፍት ይንቀሳቀሳል። የኦነግ ሊቀ-መንበር የሆኑት ዳውድ ኢብሳ ከዚህ ቀደም ኦነግ ከአሁን በኋላ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል የለውም በማለት በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ኃይል የኦነግ ጦር እንዳልሆነ ጠቁመው ነበር።

ይሁን እንጂ ምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ኃይል የጦር መሪ እንደሆነ የሚታመነው ኩምሳ ዲሪባ (ጃል መሮ) የመንግሥት እና የሃገር ሽማግሌዎችን ጥሪ ሳይቀበል ቀርቶ በትጥቅ ትግል እንደሚቀጥል ተናግሯል።

በተደጋጋሚ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል አይኖርም እየለ መግለጫ ሲሰጥ ነበረው መንግሥትም፤ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ በማሰማራት የአካባቢውን ደህንነት ለማረጋጋጥ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ይነገራል።

ይሁን እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎች የመንግሥትን የጸጥታ ኃይልም ሆነ በስፍራው ይንቀሳቀሳሉ የሚባሉት ታጣቂ ኃይሎች ላይ ቅሬታውን ሲያሰማ ቆይቷል።

ሌላው የጊዳሚ ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ በአከባቢው ባለው የደህንነት ስጋት ምክንያት ህዝቡ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በፊት ወደየቤቱ እንደሚገባ ያስረዳሉ። እኚሁ ነዋሪ እሁድ ምሽት ስለተገደሉት ሰዎች አሟሟት ተጠይቀው ሲናገሩ "ሁሉም በጊዜ ስለሚገባ ምን እንደተፈጠረ ማወቅ ከባድ ነው" ብለዋል።

አክለውም የገጠሩም ሆነ የከተማ ነዋሪ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ነው የሚገኙት። ነጋዴው ወደ ሌላ ከተማ እየሸሸ ነው። አርሶ አደሩም ከገጠር ወደ ከተማ እየሸሸ ነው በማለት በደህንነት ስጋት በነዋሪ ውስጥ የተከሰተውን ጭንቀት ያስረዳሉ።

እሁድ እለት የተገደሉት አቶ ነጋሽ በከተማዋ ታዋቂ ነጋዴ እንደነበሩ እና ባደረባቸው የደህንነት ስጋት ከጊዳሚ ከተማ በመሸሽ ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ለማድረግ ቤት አያስገነቡ እንደነበር ከነዋሪዎች ተሰምቷል።

"አቶ ነጋሽ የቤተ-ክርስቲያን አገልጋይ ነበር። የፖለቲካ ተሳትፎ ያልነበረው ሰላማዊ ሰው ነበር" በማለት አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰላሙን አጥቷል የሚሉት ነዋሪው፤ "ህዝቡ መሸሸጊያ አጥቷል" ይላሉ።

ሌላው የጊዳሚ ከተማ ነዋሪ የነበሩትና በአሁኑ ጊዜ ቤት ንብረታቸውን ጥለው አዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት አርሶ አደር ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ''ነዋሪው ቀን ላይ በአንድ ጥይት፤ ምሽት ላይ ደግሞ በሌላ ጥይት እየተገደለ ነው። ህዝብ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ነው የሚገኘው'' ብለዋል።

"አርሶ አደሩ ከቡና እርሻው አረም አየነቀለ አይደለም። እርሻውንም ማረስ አልቻለም" የሚሉት እኚሁ ነዋሪ በቡና ምርቱ በስፋት የሚታወቀው የገጠር ነዋሪው እርሻ እና ንብረቱን ጥሎ በስፋት ወደ ከተማ እየተሰደደ መሆኑን ይናገራሉ።

"ሰው ሰርቶ እየበላ አይደለም። ወላጅ ልጆቹን ትምህርት ቤት ልኮ ማስተማር አልቻለም። በቀጣይ ዓመት ገበሬው የሚበላው አጥቶ የመንግሥት እርዳታን መጠበቁ አይቀርም " ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

"ከላይ እና ከታች የሚነድበት ዳቦ ሆነናል"

"አንድ ሰው ለመንግሥት ወግኖ ከተናገረ ጫካ ያሉት እርምጃ ይወስዱበታል። ለኦነግ ከወገነ ደግሞ መንግሥት እርምጃ ይወስዳል" በማለት ሌላኛው ነዋሪ ህዝቡ የገባበትን አጣብቂኝ ይናገራሉ።

"የመታሰር እድል እንኳን አይገኝም። ሰማንያ በመቶ የመገደል እድል ነው ያለው" በማለት እኚሁ ነዋሪ ይናገራሉ።

"ሌላ ሦስተኛ አካል መፍትሄ ካልሰጠን በስተቀር፤ ከእነዚህ ሁለት አካላት መፍትሄ ይገኛል ብሎ መጠበቅ አይቻልም" ብለዋል።

ከዚህ በፊት በምዕራብ ወለጋ በተለያዩ ጊዜያት በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በነዋሪዎች ላይ ከደረሱ ጉዳቶች በተጨማሪ የአካባቢው መስተዳደር አመራሮችም መገደላቸው ይታወሳል።

በቅርቡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከመንግሥት የጸጥታ አካላት ዉጪ በክልሉ ሌላ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል እንዳይኖር ለማድረግ እየሰራ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ አማርኛ


Report Page