#ETH

#ETH


የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሶስትዮሽ የሚኒስትሮች ስብሰባ በካይሮ እየተካሄደ ነው!

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን የሶስትዮሽ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በግብጽ ካይሮ ዛሬ መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም በመካሄድ ላይ ነው።

ስብሰባው በዋናነት የሶስቱ ሀገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ዓመት መስከረም እና የካቲት 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ካደረጉት እና የግድቡን የውሃ አሞላል እና አለቃቅ በተመለከተ ከተደረገው ውይይት የቀጠለ ነው።

በስብሰባው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በቅን ልቦና እና በመተባበር ፍላጎት ያደረገችውን ጥረት ገልጸዋል።

የዚህ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል በጉዳዩ ላይ የሚደርሰው መግባባት የሶስቱንም ሀገራት እኩል ጥቅም ለማስከበር ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ስብሰባ ሶስቱ ሀገራት በቀሪ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በሶስቱ ሀገራት ሳይንቲስቶች ቡድን የቀረቡለትን ሪፖርት እና ምክረ-ሃሳቦች ተመልክቶ የወደፊት አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሆነ አመላክተዋል።

በዚህም ረገድ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረጉ ትብብሮች እና የሚቀርቡ ሃሳቦች በሶስቱ ሀገራት የተቋቋሙትን የትብብር ማዕቀፎች ጠብቀው መሄድ እንዳለባቸው አስገንዝበው ሶስቱ አገራት በተናጠል የሚያቀርቧቸው የመፍትሄ ሃሳቦችም ይህንኑ መስመር ተከትለው መቅረብ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የአባይ ወንዝ ዋነኛው የኢትዮጵያ የውሃ ምንጭ እንደመሆኑ የውሃው አጠቃቀም የአገሪቱ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ የምትከተለው አቅጣጫ የራሷን መብት እንዲሁም የጎረቤት አገራትን ህዝቦች ጥቅም የጠበቀ እንዲሆን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታለች ብለዋል፡፡

የህዳሴው ግድብን አስመልክቶ በሱዳን፣ ግብጽ እና ኢትዮጵያ መካከል የሚደረገው የሶስትዮሽ ምክክር የተፋሰሱን ሀገራት በውሃው የመልማት እና የመጠቀም መብትም የሚያረጋገጥ እና ትብብርንም የሚያጎለብት መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ሚኒስትሩ የህዳሴ ግድብ ከተጀመረ ጀምሮ ሶስቱ ሀገራት የመጡበት መንገድ ስኬት የተመዘገበበትና በሀገራቱ መካከል ይበልጥ መቀራረብን እንደፈጠረ ገልጸዋል።

የግብጹ የውሃ ሚኒስትር ዶ/ር ሞሐመድ አብድል አቲ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ትብብር ለሌሎች አገራትም አርአያ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ በህዳሴው ግድብ አሞላል እና የውሃ አለቃቀቅ ላይ የሚደረግ ውይይት የሶስቱንም አገራት ጥቅም መሰረት ያደረገ እንዲሁም ሶስቱም ወገኖች አሸናፊ የሚሆኑበት እንዲሆን መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ባለፉት ስምንት አመታት በህዳሴው ግድብ ላይ የተደረጉት ውይይቶች የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳላመጡ ገልጸው አዲስ ሃሰቦችን ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የሱዳኑ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር ሞሐመድ አባስ በበኩላቸው፣ በሱዳን እና ኢትዮጵያ ባልደረቦቻቸው ስለቀረበላቸው የእንኳን ደህና መጡ መልዕክት ምስጋና አቅርበው ከሚኒስትርነት ሹመታቸው በፊት ያከናውኗቸው የነበሩ የድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሃብቶች አስተዳደር ስራዎች በሶስቱ እህትማማች አገራት ውይይት ላይ ገንቢ አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ በተግባር ከሚያውቋቸው የሌሎች የድንበር ተሻጋሪ ወንዝ አገራት ትብብር ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የጀመሩት ትብብር ስኬታማ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህ የሶስቱንም አገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ ስኬታማ የትብብር ማዕቀፍ በተጀመረው መልኩ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል አገራቸው የሚጠበቅባትን እንደምትወጣ ገልጸዋል፡፡

ምንጭ:- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

Report Page