#ETH

#ETH


በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ በመግባት ብጥብጥና ሁከት ሊያስነሱ ነበር የተባሉ ወጣቶች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን፣ የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ወጣቶቹ የተያዙት በአይሱዙ ቅጥቅጥ አውቶብስ ተጭነው ወደ ከተማው ሊገቡ ሲሉ ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ኬላ ላይ በፀጥታ ኃይል መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹት፣ የከተማው የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ ሽብሩ ናቸው፡፡

ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት ወጥነው ሲንቀሳቀሱ የከተማው መግቢያ ላይ የተያዙትን ወጣቶች በተመለከተ አስቀድሞ ለፀጥታ ኃይል የደረሰ መረጃ በመኖሩ፣ በቀላሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቶ ተፈራ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከተማዋን የጦርነት አውድማ›› ለማድረግ የሚፈልጉ ኃይሎች ለወጣቶቹ ገንዘብ ከፍለው እንዳሰማሯቸው ገልጸዋል፡፡ በቅጥቅጥ አውቶብስ ተጭነው ወደ ከተማዋ ሊገቡ ሲሉ የተያዙት እነዚህ ወጣቶች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በእጃቸው የያዙት ዱላም ሆነ ሌላ መሣሪያ እንዳልነበረ፣ ከእነሱ አንደበት በተወሰደ መረጃ መሠረት ግን ከተማው ውስጥ ከገቡ በኋላ አስፈላጊውን መሣሪያ በተሰጣቸው ገንዘብ ለመግዛት ተስማምተው ጉዞ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡

ወጣቶቹ በቁጥጥር ሥር በዋሉ ማግሥት ማለትም ረቡዕ ጳጉሜን 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ ጅማ ከተማ ለመግባት ሌላ ሙከራ ያደረጉ የተደራጁ ወጣቶች፣ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቶ ተፈራ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹ ለሁለተኛ ጊዜ የተያዙት ታካሚ በመምሰል በአምቡላንስ ተጭነው ወደ ከተማዋ ለመግባት ሲሞክሩ ነው ብለዋል፡፡ አሽከርካሪው ከአምቡላንሱ በፍጥነት ወርዶ ከአካባቢው እንደተሰወረና አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ከሦስት ቀናት በፊት የተለያዩ የረብሻ ምልክቶች ነበሩ ያሉት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው፣ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ የአካባቢውን ሰላም የመበጥበጥ ተልዕኮ ያላቸው አካላት የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነችውን ጅማ ከተማ ሰላም ለማደፍረስም ወጣቶችን ከተለያዩ አካባቢዎች በማደራጀት፣ ወደ ከተማዋ እንዲገቡና አንዱን ከአንዱ እንዲያጋጩ የሚያደርጉት ጥረት አይሳካም ብለዋል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ እየተላለፈ የሚገኘው ሐሰተኛ መረጃ ግን የከተማዋን ገጽታ እንዳያበላሽ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ‹‹አንድ ካህን መስዋዕት ሆነዋል ተብሎ በፌስቡክ ወሬው ሲናፈስ፣ እሳቸው ከእኛ ጋር ውይይት እያደረጉ ነበር፤›› ያሉት አቶ ተፈራ፣ እንዲህ ያሉትን መረጃዎች የሚለቁ የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ግለሰቦች በነዋሪዎችም ላይ ግራ መጋባትና ጭንቀትን እየፈጠሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹የማርያም ቤተ ክርስቲያን ልትቃጠል ነው ሲባል ቤተ ክርስቲያኗን ለመጠበቅ የወጣው ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን ሙስሊሙም ነው፤›› በማለት፣ በከተማዋ ምንም ዓይነት ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ችግር አለመኖሩን፣ ሽብር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ግን ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው ለመንቀሳቀስ እንደሚሞክሩ አስገንዝበዋል፡፡

አክለውም ረቡዕ ጳጉሜን 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ላይ ተከስቶ የነበረው የእሳት አደጋ፣ ከዘርና ከሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

የጅማ ከተማ ዋና የንግድ ቦታ በሆነው መርካቶ አካባቢ በተከሰተው የእሳት አደጋ 12 ሱቆች የተቃጠሉ መሆናቸውን፣ ሱቆቹ የሁሉም ብሔር አባላትና የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች ንብረት የነበሩ ናቸው ብለዋል፡፡

በደረሰው ቃጠሎ 11 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እንደወደመም የከተማው ፖሊስ አስታውቋል፡፡ ከአንደኛው ሱቅ ውስጥ በተከሰተ የኤሌክትሪክ ገመድ ችግር ቃጠሎው ሳይከሰት እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡

የከተማውን ነዋሪዎች ሰላም ለማስጠበቅ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ አድማ በታኝና የከተማው ፖሊስ ንቁ ጥበቃ እንዲያደርጉ በየዞኑ ተዋቅረው እየሠሩ መሆኑን አቶ ተፈራ ተናግረዋል፡፡

REPORTER

Report Page