#ETH

#ETH


በመጪው የአውሮፓ ዓመት ለሚካሄደው የ2020 የማንዴላ የወጣት አፍሪካዊያን መሪዎች ዋሽንግተን ፌሎውሽፕ መርሐ ግብር ምዝገባ ተጀመረ።

‘የማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሽፕ’ የተባለው መርሃ ግብር ወጣት አፍሪካዊያንን በመመልመል በአሜሪካን አገር በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሶስት ወራት የሚዘልቅ የአመራርነት ስልጠና የሚሰጥበት ነጻ የትምህርት እድል ነው።

በኢትዮጵያ የአሜሪካን ኤምባሲ ዛሬ በሰጠው ማብራሪያ በአውሮፓዊያን ቀመር በመጪው ዓመት ለሚሰጠው መርሐ ግብር ምዝገባው ትናንት ተጀምሯል።

ምዝገባም እንደ አውሮፓ አቆጣጠር አስከ ጥቅምት 9 ቀን 2019 ይቆያል ተብሏል።

በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ2014 የተጀመረው ይህ መርሃ ግብር ወጣቶቹ በአሜሪካን መንግስት ሙሉ ድጋፍ የሚሰለጥኑ ሲሆን በሰለጠኑበት መስክ ወደየአገራቸው ተመልሰው የወጡበትን ማኅበረሰብ ያገለግላሉ።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የባህል አታሼ ከርሚሊያ ማክፎያ ዛሬ በጉዳዩ ላይ በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ ማዛግብተ ኤጀንሲ በዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ለሚፈልጉ ወጣቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም የመጀመሪያ ደግሪ ያላቸውና እድሜያቸው ከ25 እስከ 35 ዓመት የሆኑ ወጣቶች ያለምንም አካላዊ፣ በብሄር፣ በአካባቢና በማንነት ልዩነት ማመልከት እንደሚችሉ አስረድተዋል።

በዘንድሮው መሐር ግብር 700 አፍሪካዊያን ይሳተፋሉ ተብሎ በሚጠበቅበት መርሃ ግብሩ በቢዝነስ ስራ አመራር፣ በሲቪክ ስራ አመራርና በህዝብ ስራ አመራር ሶሰት መስኮች ስልጠናውን ይሰጣል ሲሉ ገልጸዋል።

ከአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በዋሽንግተን የሚደረገውን የሶሰት ቀናት አጠቃላይ ስብሰባን ጨምሮ የውድድር ዕድሉን የሚያገኙ ወጣቶች ቢያንስ ለሰባት ሳምንታት በአሜሪካ ቆይታ ይኖራቸዋል።

አመልካቾች በድረ ገጽ ተመዝግበው፣ በአካል በሚደረግ ቃለ መጠይቅ የሚለዩ ሲሆን የትምህርት ማስረጃ፣ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ፣ የስራ ልምድ፣ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለአመልካቹ የተሰጡ የምስክርነት ደብዳቤና ዕውቅናዎች ለምልመላው አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ተብሏል።

ትናንት የተጀመረው መርሃ ግብሩ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2019 እንደሚቀጥል፣ ከጥር እስከ የካቲት የቃለ መጠይቅ፣ በመጋቢት ወር አሸናፊዎችን የመለየት ስራ፣ በግንቦት ወር የቪዛ ሂደቱ ማጠናቀቅ ስራ ተከናውኖ በመጨረሻ በሰኔ ወር 2020 አሸናፊዎች ወደአሜሪካ እንደሚያቀኑ ተገልጿል።

የዕድሉ ተጠቃሚዎች የሶሰት ወራት ቆይታቸው ሲጠናቀቅ ወደአገር ቤት መመለስ ግዴታቸው ነው ተብሏል።

የሚሰጣቸው የጉዞ ሰነድም ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ በ30 ቀናት ውሰጥ አሜሪካን ለቀው እንዲወጡ የሚያስገድድ መሆኑም ተጠቁሟል።

#ENA

Report Page