#ETH

#ETH







ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ ታካሂዳለች። ምርጫውን አሳሳቢ ያደረገው ላለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያን ሲንጣት ከቆየው ሕዝባዊ ዓመፅ ቀጥመምጣቱ ብቻ ሳይሆን፤ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ተከፋፍሏል ተብሎ በተሠጋበት፤ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ፉክክሩ እንገባለን ባሉበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ ነው።

ምርጫው ምናልባትም ከምርጫ 1997 ዓ.ም ወዲህ ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበትና የአገሪቷን መጪውን እጣ ፈንታ ይወስናል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፤ ምርጫው ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተካሂዶ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ወደ መንበረ ዙፋኑ እንዳይመጣ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግዳሮቶች ይኖሯሉ በሚል በብዙዎች ዘንድ ሥጋት አንዣቧል። ሥጋቶቹ ምንድ ናቸው? መፍትሄዎቹስ? በማለት የተለያዩ የፖለቲካ ምሁራኖችን አነጋግረናል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና የብሉ ናይል የውሃ የምርምር ተቋም ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር ፈረደ እንደሚገልፁት፤ በአፍሪካ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሽንፈታቸውን በፀጋ ስለማይቀበሉና ገዢው ፓርቲ በበኩሉ በምርጫው ቢሸነፍም ሽንፈቱን በፀጋ ተቀብሎ ሥልጣኑን በሰላማዊ መንገድ ስለማያስረክብ በቅድመና በድህረ ምርጫ ግጭቶች ይቀሰቀሳሉ። በኢትዮጵያም ከመቼውም ጊዜ የገዘፉ ችግሮች ስላሉ በ2012 ዓ.ም የምታካሂደው ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ቢካሄድ ግጭቶች የሚባባሱበት ሁኔታ ያጋጥማል።

እርሳቸውም እንዳብራሩት፤ በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት በተከሰተ የፖለቲካ ትኩሳት ግጭት ላይ የነበረ የማህበረሰብ ክፍልና አካባቢ አለ። በእነዚህ አካባቢዎች በማህበረሰቡ መካከል ያለው ችግር ተፈትቶ እርቀ ሰላም ሳይወርድ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ፤ የበፊቱ ቁርሾ ሳይሽር ወዲያውኑ ወደ ሌላ ግጭት ሊገባ ይችላል። በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊና ማህበራዊ መፈረካከስ ካልተስተካከለ በቅድመና በድህረ ምርጫ ከመንግሥት ቁጥጥር በላይ የሆኑ ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ።

ከዚህ ባሻገር፤ በኦሮሚያ ክልል ላይ ኦነግ፣ በትግራይ ክልል ላይ ህውሐት፤ እንዲሁም በአማራ ክልል ላይ አብን ሙሉ ለሙሉ ቢመረጡ እነዚህ ኃይሎች ልዩነታቸውን አጥብበው መንግሥት መመስረት ይችላሉን? ቢባል እነዚህ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን ወደጎን በመተው አንድ በሚያደርጋቸው ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው ለመሥራት ቁርጠኝነት ይኖራቸዋል ብሎ ለመገመት ያስቸግራል። መንግሥት መመስረት ካልቻሉ ደግሞ አገር መንግሥት አልባ ትሆናለች። ይህ ምናልባትም አገሪቷን እንደ ቀድሞዋ ጎረቤታችን ሶማሊያ ሁለተኛዋ መንግሥት አልባ አገር ሊያደርጋት እንደሚችል ገልፀዋል።

“ጫካ ገብቶና በተለያየ አገር ተሰድዶ የነበረው ወታደር፤ ተቃዋሚ ኃይልና የፖለቲካ ስደተኛ ከማህበረሰቡ ጋር እንዲላመድ፤ ወገን በወገኑ ላይ መተኮስ እንዲያቆም፤ ትጥቁን በኃይል ሳይሆን በፈቃደኝነት እንዲፈታና ማህበረሰቡን ተቀላቅሎ ሲቪል ማህበረሰብ እንዲሆን የማድረግ ሥራ በሰፊው አልተሰራም” የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ “በየክፍለ አገሩ የኦሮሞ፣ የአማራ፤ የትግራይ፤ የአፋር ወ.ዘ.ተ ራሳቸውን ነፃ አውጭ ግንባር ብለው ሰይመው ታጥቀው የተቀመጡ ልዩ ልዩ ኃይሎች ቀድሞ መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል” ይላሉ።

የታጠቀ ኃይል ትጥቁን ፈትቶ ማህበረሰቡን ባልተቀላቀለበት፤ በአገር ውስጥ በየጎራው ጦር እየተሰበቀ የጦርነት አዋጅ በሚታወጅበት፤ ማህበረሰቡ በውይይት ሳይሆን በጦር መሣሪያ ችግሮቹን ሁሉ ካልፈታሁ በሚልበትና በኃይል ችግሮቹን ለመፍታት ዝግጁ በሆነበት ወቅት እንዴት ተደርጎ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ወደፊት ሊመጣ ይችላል? በማለት ይጠይቃሉ።

ከውስጥ ካለው አገር አፍራሽ ኃይል ባለፈ በቀጠናው ያለው አለመረጋጋት በምርጫው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል። በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያለው የአልሻባብ እንቅስቃሴ መናቅ የለበትም። የመን እና ሶሪያን እያፈረሳቸው ያለው የጽንፈኞች እንቅስቃሴ፤ በግብጽ ያለው የአማፂያን እንቅስቃሴ፤ በኢትዮጵያ አሁን ካለው ጤነኛ ያልሆነ ውስጣዊ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ፤ እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች ምርጫውን ተከትሎ በሚከሰት ግርግር ወደ አገሪቱ ዘልቀው በመግባት የአገሪቱን ዘላቂ ሰላምና ሉአላዊነት ሊያሳጧት እንደሚችሉ ተናግረዋል። ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምርጫው ቢካሄድ መፈንቅለ መንግሥት እስከማስከተል ሊደርስ የሚችል ውጥረት በአገሪቱ ይነግሥ ይሆናል የሚል ሥጋት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ፤ “የምርጫ ሕጉ መሰረታዊና ሥር ነቀል በሆነ መልኩ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እንዲያስተናግድ ተደርጎ ሳይስተካከል፤ ገለልተኛ የሆኑ ፍርድ ቤቶችና የፍትህ አካላት በሌሉበት፤ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉት የተሳሳቱ አካሄዶችና የተዛቡ አመለካከቶች ሳይቀየሩ፤ ኢትዮጵያ ከየት ተነስታ ወዴት እንደምትሄድ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ በሌለበት፤ በየክፍለ አገሩ ያሉ አንጃዎች በሰው ደም ዙፋን ለመቆናጠጥ በሚቋምጡበት፤ ችግሩን በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ ከመፍታት ይልቅ በአፈሙዝና በኃይል ለመፍታት አሰፍስፈው ባሉበት በእነዚህ ሁሉ ችግሮች አይነተኛ መፍትሄ ተበጅቶላቸው ችግሮቹ አቅጣጫ ሳይዙ ምርጫ አካሂዳለሁ ማለት፤ አገሪቱ መንግሥት አልባ ሆና እንድትፈራርስ ማመቻቸት ማለት ነው፤” ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

በሌላ በኩል፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ስትራቴጂክ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህሩ ገብረመድህን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ ህዝቡን አንድ ከሚያደርገው ይልቅ ህዝቡን የሚከፋፍል አጀንዳ ቀርፀው የሚያራግቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መበራከት፤ በአገሪቱ ያለው ወቅታዊ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና በየቦታው የሚስተዋሉ ግጭቶች፤ ፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን ወደጎን በመተው በጋራ ለመሥራት ዝግጁ አለመሆን፤ ጽንፈኝነትና የፖለቲካ መካረር፤ መንግሥት በመደበኛ የአስተዳደር ሥርዓት መቆጣጠር አቅቶት በኮማንድ ፖስት የሚያስተዳድራቸው አንዳንድ ቦታዎች መኖራቸው፤ በየክልሉ እንደ ቄሮ፣ ፋኖ የመሳሰሉ ሕገወጥ አደረጃጀቶችና ማህበራት መበራከታቸው፤ እንዲሁም የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ምህረት ተደርጎላቸው በቅርቡ ወደ አገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገሪቷ እንዳትረጋጋ አድርገዋል። እነዚህ ሃይላት በምርጫው ጠንካራና ተፎካካሪ ፓርቲ ሆነው ለመቅረብ በቂ የዝግጅት ጊዜ አለማግኝታቸው ምርጫው ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በሠላም እንዲካሄድ እና ህዝብ ያመነበት መንግሥት እንዳይመጣ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ስለዚህ ባለው ጊዜ ከላይ የተጠቀሱትን ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዳይሆን የሚያውኩ ችግሮችን ቀድሞ እልባት በመስጠት፤ ምርጫውን በተያዘለት መርሐ ግብር በማካሄድ በህዝብ የተመረጠ እና ህዝብ ያመነበት መንግሥት ወደ ሥልጣን እንዲመጣ በማድረግ፤ ምርጫውን አንድ የግጭት መፍቻ መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም በአገሪቱ የተጋረጡ ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ህዝብ ያመነበትና ህዝብ የመረጠው መንግሥት ሊመሰረት የሚችልበት ብቸኛ መንገድ ምርጫ ስለሆነ፤ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መካሄድ ይኖርበታል። ነገር ግን ምርጫው በተያዘለት ጊዜ የማይካሄድ ከሆነ አለመካሄዱ በራሱ ራሱን የቻለ ችግር የሚያስነሳ መሆኑን ነው መምህር ገብረመድህን የሚናገሩት፤

“ፓርቲዎች ህዝቡን ከሚያለያዩ ይልቅ ህዝቡን አንድ በሚያደረጉ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው በመሥራት፤ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ተካሂዶ የህዝብ ይሁንታ ያገኝ መንግሥት ወደ ሥልጣን ካልመጣ፤ አሁን ላይ በአገሪቱ የሚስተዋለው አለመረጋጋትና ብጥብጥ ወደማይቀለበስ ደረጃ ሊሸጋገር ይችላል” የሚል ሥጋት እንዳላቸውም ያመለክታሉ።

ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ተካሂዶ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ወደ ሥልጣን ካልመጣ አሁን ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱን ያሳጣዋል። ይህ ደግሞ አገሪቷ እንዳትረጋጋ ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል። እንዲሁም፤ ህዝብ የመረጠውና ህዝብ የተቀበለው መንግሠት ከሌለ በአገሪቱ ብጥብጥ ለማስነሳት የሚፈልጉ ኃይሎች እንደ ምክንያት በመውሰድ ግጭቶችን ለማስነሳት መንገድ ይከፍታል ብለዋል።

በአንፃሩ፤ እንደ ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር እምነት በአገሪቱ የተሳካ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና እውነተኛ ምርጫ ተካሂዶ የህዝብ ይሁንታ ያገኘና የተመረጠ መንግሥት ወደ መንበረ ዙፋኑ እንዲመጣና አገር አንድ ሆና እንድትቀጥል ከተፈለገ ከምርጫው በፊት መከናወን ያለባቸው በርካታ ተግባራቶች አሉ ይላሉ።

ከእነዚህ መካከል፤ ኢትዮጵያ ከየት ተነስታ ወዴት እንደምትሄድ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ ሊኖር ይገባል። በመቀጠል በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በህብረተሰቡ መካከል ያለው ልዩነት ጠቦ የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን አገር ሠላሟ እንደተጠበቀ እድትቀጥል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በስፋት መሥራት ይጠይቃል። የምርጫ ህጉ መሰረታዊና ሥር ነቀል በሆነ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በሚያስተናግድና የፖለቲካ ትኩሳቱን በሚያበርድ መልኩ ሊስተካከል ይገባል። እንዲሁም፤ ገለልተኛ የሆኑ ፍርድ ቤቶችና የፍትህ ተቋመት ሊኖሩ እና በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉትን የተዛቡ አካሄዶችና አመለካከቶች የሚቀይሩ አሠራሮች ሊኖሩ ይገባል።

ጫካ ገብቶና በተለያየ አገር ተሰዶ የነበረው ወታደር፣ ተቃዋሚ ኃይልና የፖለቲካ ስደተኛ ከማህበረሰቡ ጋር እንዲላመድ፤ ወገን በወገኑ ላይ መተኮስ እንዲያቆም፤ ትጥቁን በኃይል ሳይሆን በፍቃደኝነት እንዲፈታና ማህበረሰቡን ተቀላቅሎ ሲቪል ማህበረሰብ እንዲሆን የማድረግ ሥራ በሰፊው ሊሠራ ይገባል። እንዲሁም በየጎጡ እራሱን ነፃ አውጭ ግንባር ብሎ በመሰየም በሰው ደም የሥልጣን ጥሙን ለማርካት የሚቋምጠው ጎጠኛ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ሥልጣን ወደሚይዝበት ጎዳና እንዲመጣ የሚያስችል የሰላም ኮንፈረንሶች ሊካሄዱም ይገባል።

ችግሮቹን ሁሉ በውይይት ሳይሆን በጦር መሣሪያና በአፈሙዝ ካልፈታሁ የሚለውን የማህበረሰብ ክፍል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠና በመስጠት በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ተወያይቶ ችግሩን የሚቀርፍበት መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ስለዚህ ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ አገር አንድ ሆና እንድትቀጥል ከተፈለገ፤ ምርጫው ከመደረጉ በፊት ሊሠሩ የሚገባቸው የቤት ሥራዎች ቀድመው ሊሠሩ እንደሚገባ ፕሮፌሰሩ አሳስበዋል።

በአጠቃላይ፤ እንደ ባለሙያዎቹ እምነት ምርጫውን የሚያወኩ አንኳር ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራና ህዝቡን አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ከተቻለ በአገሪቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ሊመጣ ይችላል። በዚህም ማህበረሰቡ ርዕስ በርዕስ ከመበላላትና ከመጠፋፋት ሊድን ይችላል። አገሪቷ ከገባችበት ቀውስ ወጥታ ወደ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልትሸጋገር ትችላለች።

ነገር ግን፤ ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች አይነተኛ መፍትሄ ሳይበጅላቸው ምርጫው በተቀመጠለት ቀነ ገደብ የሚካሄድ ከሆነ፤ ህዝቡ ወደ ርዕስ በርዕስ ጦርነት በማምራት አገሪቷ የወንበዴዎች መፈንጫ የምትሆንበት፤ የግፍ የደም ጽዋ የሚፈስባት፤ እንዲሁም አገሪቷ መንግሥት አልባ ሆና ዜጎች አገር አልባ የሚሆኑበት አደጋም ሊፈጠር ይችላልና በምክንያን ውጤት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መስጠት ያስፈልጋል።

Report Page