#ETH

#ETH


የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በከተማዋ ቀጣይ የትኩረት አቅጫዎች ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጡ ።

የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞታቸውን በማስቀደም የከተማዋን የ2012 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ከንቲባው አዲሱ አመት የሰላም የብፅግናና የአብሮነት እንዲሆን በመግለፅም ነው።

ስለ ከተማዋ ውብ ፅዱና አረንጓዴ ገፅታ መላበስን ብሎም ምርጥ የቱሪዝም እና የኢቨስትመንት መዳረሻነት አያይዘው ያስረዱት ከንቲባው ይህም በሚቀጥሉት አመታትም ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነ በማስረዳት ነው።

ይህ የከተማዋ ጽዳትን እና አረንጓዴ ገጽታን እንዲሁም የምትታወቅበትን ምቹ የቱሪዝምና እና የኢንቨስትንት ተመራጭነት ባለፉት ወራት ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት ተጽእኖ እንደፈጠረ ከንቲባው በመግለጫቸው አያይዘው አስረድተዋል።

ይህ ተከስቶ የነበረ የጸጥታ ችግር ዳግም በከተማዋ እንዳይታይ የሰላሙ ባለቤት ከሆነው ህዝብ ጋር በመቀናጀት የሚያከናውኑት ተግባር እንደሆነም አቶ ጥራቱ በመግለፅ የተናገሩት ለዚህም አሁን ላይ ያለውን መደላደል እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም እንደሆነ አስረድተዋል።

ከዚህ አንጻር የከተማዋን ወጣቶች ቀደም ሲል ከተማ አቀፍ ክብረ በዓላትን ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቁ የነበራቸውን ሚና ለዘላቂ ሰላምና ደህንነት አስተዳደሩ ይበልጥ እንዲጎለብት ትኩረቱን የሚያደርግ ይሆናልም ብለዋል።

አሁን ለይ ይህ የከተማዋ ሰላማዊ ገጽታን የትኛውም ጎብኚም ሆነ የሚዲያ ተቋም ተዘዋውሮ መመልከትን ጨምሮ መታዘብ የሚችል እንደሚሆን በመግለጫቸው ከንቲባው አክለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የህብረተሰቡን አንድነት የሚሸረሽሩ ብሎም ጥርጣሬዎች የሚዘሩ መረጃዎችን በተባባረ ክንድ ለመቋቋም ይቻል ዘንድ ትኩረታቸውን እንደሚያደርጉም ነው አቶ ጥራቱ የጠቆሙት፡፡

ሌላው በ2012 አዲስ አመት ትኩረት ሰጥተው ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል የሲዳማ ብሔር በክልል የመደራጀት ጥያቄን ህገመንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ ህዳር 3 ህዝበ ውሳኔን የተመለከተ ተግባር ይሆናል ብለዋል።

በዚህም በእለቱ የሚደረገው ምርጫ ሰላማዊ ፍትሀዊ እና ያለ ምንም እንከን የሚጠናቀቅ እንዲሆን አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት የሚሰራው ይሆናልም ብለዋል፡፡

ለዚህም ያሉት ውስን ሁለት ወራት መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባው እንደ ከተማ አስተዳደሩ ሰላምን እና ደህንንትን በማረጋገጥ እንዲሁም ህጋዊነቱን ጠብቆ ተጨማሪ ምንም አይነት የህይወት መስዋዕትነት ሳያስከፍል የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ዋነኛው ተግባራቸው ስለመሆኑም ከንቲባው በመግለጫቸው አመላክተዋል።

ተያይዞም ህግ የማስከበር ጉዳይ ሌላኛው የአስተዳደሩ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ የገለጹት ከንቲባው ይህም ከባለፈው አመት ጀምሮ በልማት ስራዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ስለመፍጠሩ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ በተለይም በከተማዋ ተከስቶ የነበረን አለመረጋጋት ተከትሎ በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች የሚስተዋሉ ህገወጥ የንግድ እና የመሬት ወረራዎችን ብሎም ግባታዎችን በማስከበሩ ረገድ ተግባራዊ ይደረጋል በማለት ነው ከንቲባው ያስረዱት፡፡

ለዚህም የህበረተሰቡ ድርሻ ምን መሆን አለበት የሚለውን ከወዲሁ ትኩረት በመስጠት እና እስከታችኛው መዋቅር ድረስ አስፈላጊውን ውይይት በማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን እውን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቶች እየተከናወኑም ናቸው ብለዋል፡፡

ሌላው የወጣቱ የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተ ያለው ተግባር ይገኛል ያሉት ከንቲባው በዚህም በተለይም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚገኙ ወጣቶች ወደ ስራ ማስገባት ላይ ያነጣጠረ ይሆናልም በማለት አስረድተዋል፡፡

በዚህ ረገድ ከተለመደው አሰራር በመውጣት በሚቀጥለው በጀት አመት አዳዲስ ፕሮጄክቶችን በመቅረጽ እንዲሁም የሌሎች ከተሞችን ተሞክሮዎች በመውሰድ የሚተገበርም ይሆናል በማለት ነው ከንቲባው የገለጹት፡፡

ከዚህ ቀደም ለወጣቱ የስራ እድል ከመፍጠር አንጻር ሲደረጉ ነበሩ ድጋፎች እና የብድር አቅርቦቶች ምንም እንኳን ያመጧቸው መልካም የሚባሉ ተግባራት ቢኖሩም ከመስሪያ ቦታ አቅርቦት አንጻር የነበሩ ሼዶችን ለስራ አጥ ወጣቶች ከማስተላላፍ ይልቅ በተለያየ የሙያ መስመር ተሰማርተው ገቢ ያላቸው የህበረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ የተደረጉበት አሰራርን በመቅረፍ ጭምር የሚሰራ እንደሚሆን ነው አቶ ጥራቱ ተናገሩት፡፡

ከጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች እና ህጻናት አንጻር የሚከናወኑ ተግባራ ሌላኛው የአስተዳደሩ የትኩረት አቅጣጫ ስለመሆናቸው ለጋዜጠኞች በመግለጫቸው የጠቆሙት ከንቲባው በዚህ ረገድ ቀደሞ የነበረውን በአንድ ማእከል በማጎር የሚከናወን ተግባርን ታሳቢ ያላደረገ ስለመሆኑም በመግለጽ ነው፡፡

በመሆኑም አስተዳደሩ ለዘላቂ መፍትሄ አካል ሊሆን የሚችል አሰራርን በማጥናት እድሚያቸው ለስራ የደረሱ ወጣቶችን ስልጠና በመስጠት የራሳቸውን ኑሮ መምራት የሚችሉበትን ሁኔታ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እውን ማድረግ እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡

በተመሳሳይም እድሜያቸው ለስራ ያልደረሱ ህጻናትን በተመለከተ የህብረተሰቡ ንቁ ተሳፎን በማከል ወደ ተሻለ ኑሮ ማምጣት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡

ኢንቨስትመንትን እና የቱሪዝም መዳረሻነትን ከማረጋገጥ አንጽር ባለፉት አመታት ከተማዋ ከሀገር አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ ማዕከል ለማድረግ በርካታ ስራዎች ስለመከናወናቸው የተቆሙት አቶ ጥራቱ በዚህ ረገድ በዋናት ሀዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተጠቃሽ እንደሆነ በማስገንዘብ ነው፡፡

ስለሆነም በሚቀጥለው በጀት አመት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች እንወዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኩ ተሰማርተው የሚገኙ ኩባኒያዎች ሳይቀሩ በከተማዋ መጠነ ሰፊ ተሳትፎአቸውን እዲያደርጉም ተናግረዋል።፡

ከዚህ አንጽር ልማታዊ ባለሀብቱ በከተማዋ የሚያነሷቸው ስጋቶች ስለመኖራቸው ያስታወሱት ከንቲባው ለዚህም ከደህንነት እና ከሰላም ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን በመቅረፉ ረገድ የሚከናወኑ ተግባራትን ሰላም ወዳድ ከሆነው ህዝብ ጋር በመሆን ከዳር ለማድረስ ጥረት ይደረጋል በማለት አስረድተዋል፡፡

ልማታዊ ባለሀብቱን እንደ ከተማ ለመጠቀም ሲታሰብ አንድም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን እንደ ሀገር ስለሚያስገኝ በሌላም የስራ እድል የሚፈጥር ከመሆኑ ጋር የሚተሳሰር እንደሆነ የገለጹት ከንቲባው በተመሳሳይም ባለሀብቱ በከተማዋ ለማልማት አለመቻሉን በማመላከት ገጽታን የሚጎዳ እንደሆነ በማስረዳት ነው ከንቲባው ለጋዜጠኞች ያስረዱት፡፡

ከማህበራዊ ዘርፉ አንጻር በተለይም ከትምህርት ዘርፉ ጋር ተያይዞ መምህራንን ጥቅማ ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር ወላጆች እና ተማሪዎች በዘርፉ መሪ ተዋናይ ሆነው እንዲገኙ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉም ይሆናሉ ብለዋል ከንቲባው በመግለጫቸው፡፡

በመጨረሻም አቶ ጥራቱ በመንግስት ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችንም ፍትሀዊ ቀልጣፋ እና ፈጣን ብሎም እርካታ ያለው ለማድረግ በየደረጃው በምናከናውናቸው መድረኮች አጠናክረን እንቀጥላለን በማለትም ገልጸዋል፡፡

ከንቲባ ጥራቱ የሰጡት መግለጫ ተከትሎም ከጋዜጠኞች ጥቄዎች ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡

እንደ ከተማዋ ከንቲባ በሚቀጥለው በጀት አመት ለውጥ ለማምጣት ተያዘውን የትኩረት አቅጣጫን ከዳር ለማድረስ የሚያስችል ቁርጠኛ አመራር ስለመኖሩ ያብራሩት በዚህም አብዛኛው አመራር ተልዕኮውን በትክክል መወጣት ስለመቻሉ የአስተዳደሩ አስተባባሪ ኮሚቴ መፈተሸ ችሏልም በማለት ነው ምላሽ የሰጡት፡

ሆኖም ጥቂት በሆኑ መዋቅሮቻችን ላይ የተስተዋሉ ድክመቶችን ለማረም የሚያስችል ተግባርን በተመለከተ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአዳዲስ አመራር እና በሽግሽግ ለማስተካከሎ የተደረገውን ጥረት በመጠቆምም ነው ምላሻቸውን የሰጡት፡፡

በዚህ ረገድ በተለይም እንደ ከተማ ከጸጥታ መዋቅሩ አንጻር የነበሩ ድክመቶችን ለማረም የተወሰደው ፈጣን እርምጃ ለውጡን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆንን የሚጠቁምም ነው በማለት ነው ምላሽ የሰጡት፡፡

የሀዋሳ ከተማ ባለቤትነትን አስመልክቶ ከንቲባው በመግለጫቸው ሲያስረዱም በሀዋሳ ከተማ ባለቤትነት ዙሪያ ምንም አይነት ብዥታ ውስጥ የሚያስገባ ነገር ሊኖር አይገባም ጉዳዩ የሲዳማ ህዝብን የሚመለከት ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

ከተማዋ ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁንም እንዲሁም ወደፊት የሲዳማ ብሔር ጉዳይ ነው ሆኖ የሚታየው በማለትም አክለዋል፡፡

በዚህ ረገድ የክልሉ ምክር ቤትም ሆነ ስራ አስፈጻሚው በሀዋሳ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ አቋም ያለው እና በየጊዜውም እውቅናውን ግልጽ መልስ ስለመስጠቱም ነው ከንቲባው ያብራሩት፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ብዥታን የሚፈጥሩ ከህዝበ ውሳኔ ጋር ተያይዞ በሀዋሳ ከተማ ላይ አይካሄድም የሚሉ አሉባልታዎችንም አቶ ጥራቱ ሲገልጹ ሀሳቡ ከእውነት የራቀና እና ከሲዳማ ዞን ህዝበ ውሳኔ ጋር አብሮ እንደሚካድ ከምርጫ ቦርድ መግለጫ መሰጠቱን በማስረዳት ነው፡፡

ተያይዞም በሀዋሳ ከተማ ላይ ምርጫ ቦርድ ልዩ የህግ ማዕቀፍ እንደሚኖረው የተገለጸውን አሰራርም አስመልክቶ ከንቲባው አብዛኛው ከተሞቻችን ብዝሀነትን የሚሳዩ ሆነው የመገኘታቸውን አንድምታ በማስረዳት ሲሆን በዚህም ማንኛውም ዜጋ ህገመንግስታዊ መብቱን በመጠቀም መኖር የሚስችለውን ማረጋገጫ ማግኘቱን በማከል ነው፡፡

ስለሆነም ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ የሀዋሳ ከተማን በተለየ መልኩ የሚያይ የህግ ማዕቀፍ ማውጣት ህገመንግስታዊ እንደማያደርገው ያስረዱት ከንቲባው ይህን አልፎ ለሚኖር ማንኛውም ተግባር አስተዳደሩም የራሱን አቋም የሚይዝ እንደሚሆን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ምንጭ፦ Hawassa City Administration Public Relation Office

Report Page