#ETH

#ETH


የዋጋ ጭማሪ መቆሚያው የት ይሆን?

በጤፍ ላይ በኩንታል ከ400 እስከ 800 ብር፤ በስንዴ ላይ በኩንታል ከ300 እስከ 600 ብር፤ እንዲሁም በአትክልትና ሽንኩርት ላይ በኪሎ ከ10 እስከ 18 ብር ጭማሪ መደረጉ ከታህሳስ 2011 ጀምሮ የታየ ችግር ሆኗል።

ከዓመት ዓመት መባሉ ቀርቶ ከዕለት ዕለት ከፍ ሲል እንጂ ባለበት እንኳን መርጋት የተሳነው የሸቀጦች ዋጋ ሰፊውን በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያለውን አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል እጅጉን ፈትኖታል። ለከፋ ምሬትና እሮሮም ዳርጎታል። ይህ የዋጋ ማሻቀብ ሂደትም የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከአንድ አሃዝ አልፎ ሁለት አሃዝ የደረሰ፤ ከ15 በመቶ የተሻገረ ነው። ይህ ሂደት ደግሞ በወጉ ተለይቶና ታቅዶ እንደየባህሪው ሊሰራበትና ሊፈታ ካልቻለ፤ የደላሎችና ሕገወጦችን ኪስ የሚያደልብ፤ የድሆችን ረሃብ በማጽናት ለብሶት የሚዳርግና የሰፊውን ህዝብ ትዕግስት አስጨርሶ ለአመፅ የሚያነሳሳ፤ ሕገወጦች የሰበሰቡትን ሃብት ቁጭ ብለው የሚበሉበትን ስፍራም የሚያሳጣ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።

ይሄን የተገነዘበው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ችግሩን ለማቃለል ያስችለው ዘንድ፤ የችግሩን ምክንያት፣ የችግሮቹ ባለቤቶችና እየተስተዋሉ ያሉ ተጽዕኖዎችን፣ ብሎም እየተወሰዱ ያሉና ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎችን ያመላከተ ጥናት ከሶስት ተቋማት ጋር ሆኖ አከናውኗል። ሰሞኑንም ጥናቱን መነሻ በማድረግ ከባለድርሻዎች ጋር ተወያይቶ፣ ሕገ ወጦች በሕግ አምላክ የሚባሉበትንና ለዚህም ተቀናጅቶ ለመስራት የሚቻልበትን አቅጣጫ አስቀምጧል። እኛም በዛሬው እትማችን ጥናቱን፣ ተሳታፊዎችንና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮችን ዋቢ በማድረግ ሀሳቡን በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል።

እንደ መነሻ

ህብረተሰቡ በስፋት በሚጠቀምባቸው የፍጆታ ሸቀጦች በተለይም በምግብ ሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ተከትሎ የዋጋ ግሽበቱ ወደ ሁለት አሀዝ ከፍ ማለቱ በዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ምሬትን አስከትሏል። ይሄን ችግር ለመፍታትም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን፤ ምርታማነትን ከማሳደግ ጀምሮ ለፍጆታ ሸቀጦች ላይ ድጎማ እየተደረገ ይገኛል። ለአብነት፣ ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ፣ በ2008 ከነበረው 266 ሚሊዬን 828ሺ807 ኩንታል ዓመታዊ ምርት በ2011 315 ሚሊዬን 602ሺ 58 ኩንታል መድረስ ተችሏል። የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትም ቢሆን ካለፉት ዓመታት ጭማሪ አሳይቷል።

ከዚህ ባለፈም ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ለመሙላት በዳቦ ዱቄትና ፓልም ዘይት ላይ ድጎማ የተደረገ ሲሆን፤ የዳቦ ስንዴ በወር 647ሺ 944 ኩንታል (በዓመት 7 ሚሊዬን 775 ሺ 328 ኩንታል)፣ እና ፓልም የምግብ ዘይት በወር 40 ሚሊዮን ሊትር (በዓመት 480 ሚሊዮን ሊትር) በድጎማ እየቀረበ ነው። ውጤቱ ግን በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ፤ ያለ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት በመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ የታየውን የዋጋ ንረት ያስከተለውን ችግር በመቅረፍ ሸማቹን ህብረተሰብ ከኑሮ ውድነት መታደግ ይገባል።

የዋጋ ንረቱ መንስኤዎች

ከዓመት ዓመት የግብርናው ምርታማነት እያደገና በሚታዩ ጉድለቶችም አቅም በፈቀደ የመንግስት ድጎማ ያልተለየ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ውጤት ላለመገኘቱ ምክንያት የሆኑ ነገሮችም በጥናቱ ተለይተዋል። በውይይቱም በስፋት ተነስተዋል። ከእነዚህ መንስኤዎች መካከል ደግሞ አንዱ በፍላጎቱ ልክ አቅርቦት ያለመኖሩ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ያለውን ምርትም ቢሆን በሕገ ወጥ ነጋዴዎችና ኮትሮባንድ ምክንያት ወደህብረተሰቡ እንዳይደርስ እየተደረገ መሆኑ ነው። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን ትልቅ ድርሻ እንዳለው የተለየው ደላላ ሲሆን፤ የሸቀጦች የግብይት ሂደቱ በደላላ ጣልቃ ገብነት እጅጉን የተፈጠነ ስለመሆኑ ነው በሰፊው የተነገረው።

በዚህ መልኩ የምርት አቅርቦት እጥረቱ ብሎም ምርትን ያላግባብ ማከማቸትና በሕገወጥ መልኩ የመሸጥና የደላሎች መፈርጠም ደግሞ ፍትሃዊ ያልሆነ የሸቀጦች የዋጋ ውድድርን ብሎም በራስ ጊዜ ዋጋ የመወሰን አካሄድን ፈጥሯል። የአየር በአየር ንግድንም አበራክቷል። በዩኒየኖችና ሸማች ህብረት ስራ ማህበራትም ቢሆን የሚታየው የአቅም፣ የክህሎትና የአሠራር ውስንነት እንዲሁም የስነ-ምግባር ጉድለት የችግሩ ተደማሪ ምክንያቶች ናቸው።

ሃላፊነት የተዘነጋባቸው ቦታዎች

ለእነዚህ ችግሮች በዚህ መልኩ ጎልቶ መውጣት በመንግስት ተቋማት አደረጃጀቶችም ሆነ በነጋዴውና አምራቹ የሚስተዋል ሃላፊነትን የመዘንጋት አካሄድ መኖሩም ተለይቷል። ለአብነት፣ በድጎማ በሚያቀርቡ ሸቀጦች ዙሪያ በአዲስ አበባ በሚገኙ 39 የዱቄት ፋብሪካዎች፣ 113 ዳቦ ቤቶችና ስምንት ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ላይ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጓል። በዚህም፣ ጥራቱን ያልጠበቀ ስንዴ ቀላቅሎ በመፍጨት መንግስት በድጎማ በሚያቀርበው ማዳበሪያ በመቀየር ትስስር ላልተደረገላቸው ዳቦ ቤቶች ጭምር መሸጥ፤ የድጎማውን የስንዴ ዱቄት በራሳቸው የተለየ(ስፔሻል) ዱቄት ማዳበሪያ ከረጢት በማሸግ ለገበያ በማቅረብ እስከ 2000 ብር መሸጥ፤ በሕገ-ወጥ መንገድ የድጎማ ስንዴ ትስስር ላልተፈጠረላቸው ነጋዴዎች አሳልፎ መሸጥ በዱቄት ፋብሪካዎች የታዩ ችግሮች ናቸው።

ዳቦ ቤቶችም ቢሆኑ፣ ከአርበኞች፣ ሮዛ/አፍሪካ/ እና ምስራቅ ዳቦ ቤቶች በስተቀር ከተቀመጠው ዋጋ በላይ እና በመጠንም ከግራም በታች ጋግረው የመሸጥ፤ የድጎማ ስንዴ ዱቄትን ለድፎ ዳቦ፣ ለጣፋጭ ኩኪስ፣ ዶናትና ለልዩ ልዩ ደረቅ ኬኮች ምርት በማዋልና በመሸጥ የተጋነነ ትርፍ ማትረፍ፤ አንዳንዶቹም የሚጠቀሙት የመጋገሪያ ዓይነት ጥራትና የመጋገር አቅም ዝቅተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

በሰብል ምርቶችም ሆነ በአትክልትና ፍራፍሬ ግብይትም በሕገ-ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳለ አስመስሎ አሳሳች መረጃ የመልቀቅ፤ ወፍጮ ቤቶችና እህል ቸርቻሪ ነጋዴዎች መሳለሚያና እህል በረንዳን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠር ኩንታል የጤፍ ምርትን አከማችቶ መያዝ አለ። በዚህም በጤፍ ላይ በኩንታል ከ400 እስከ 800 ብር፤ በስንዴ ላይ በኩንታል ከ300 እስከ 600 ብር፤ እንዲሁም በአትክልትና ሽንኩርት ላይ በኪሎ ከ10 እስከ 18 ብር ጭማሪ መደረጉ ከታህሳስ 2011 ጀምሮ የታየ ችግር ሆኗል። ይህ የዋጋ ጭማሪና ያልተገባ ጥቅም ፍለጋ በነዳጅ ዘይት፣ በግንባታ እቃዎችና ሌሎችም ላይ የተስተዋለ መሆኑን ነው በጥናቱም ሆነ በውይይቱ የተገለጸው።

በተመሳሳይ መልኩ፣ በመንግስት ድጎማ ከውጪ የሚገባው ፓልም የምግብ ዘይት ለህብረተሰቡ በአግባቡ መሰራጨት ሲገባው በመርካቶና ሾላ ገበያዎች ጭምር በሕገ-ወጥ መንገድ ሲሸጥ፤ በክልሎችም ሲዘዋወር ተገኝቷል። ለምሳሌ፣ አንድ መኪና ፓልም የምግብ ዘይት ደሴ ላይ፤ አራት መኪና ከነተሳቢው ወደ መቀሌ ሊገባ ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል። በአዲስ አበባም 1ሺ249 ሊትር ፓልም የምግብ ዘይት አየር በአየር ሲዘዋወር ተይዟል። የፈሳሽ ዘይትም በየቀኑ አስደንጋጭ የዋጋ ጭማሪ እየታየበት ይገኛል።

በዚህ መልኩ ለሚታየው ችግር ደግሞ የመንግስት አካላት የክትትልና ቁጥጥር መላላት ውጤት ሲሆን፤ በአመራሩና ባለሙያው ከላይ እስከ ታች ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓትን በመዘርጋት ህግ እንዲከበር ያለመከታተል ችግር ተስተውሏል። በሕገ-ወጦች ላይ አስተማሪ የሆነ የእርምት እርምጃ አለመውሰድና አለማስወሰድ፤ አልፎ አልፎም ለሕገ- ወጦች ተባባሪ በመሆን እንዳለ ተለይቷል።

የተወሰዱ እርምቶች

ችግሩን ከመከላከል አኳያ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ግብር ሃይል ተዋቅሮ በድርጊት መርሃ ግብር ተደግፎ እየተሰራ ይገኛል። በዚህም ከተፈቀደው ግራም በታች ዳቦ ጋግረው እንዲሁም ከተቀመጠው ዋጋ በላይ ጨምረው ሲሸጡ የተገኙት 76 ዳቦ ቤቶችን ከትስስር በማስወጣት ሌሎችን መልምሎ የማስገባት ስራ ተሰርቷል፤ ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ እሸጋ የሚደርስ እርምጃ በመውሰድም የማስተካከል ስራ ተጀምሯል። በመሰረታዊ ሸቀጥ ስርጭት ላይ ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ ሁለት የንግድ ድርጅቶች እንዲታሸጉ ተደርጓል።

በአዲስ አበባ አየር በአየር ሲዘዋወር የተያዘ 1ሺ249 ሊትር ፓልም የምግብ ዘይትና 1ሺ600 ኩንታል ስኳር በሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ተሸጦ ለመንግስት ገቢ ሆኗል። በሰብል ምርቶች እና አትክልትና ፍራፍሬ ግብይት ረገድም በአዲስ አበባ ብቻ ለ223 የንግድ ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፤ 86 ተቋማትን የማሸግ፣ 580 የንግድ ተቋማትን ከትስስር የማስወጣት፣ እንዲሁም ያለንግድ ፈቃድ ሲሰሩ በተገኙ የንግድ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል። በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በ14ሺ561 ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ሲወሰድ፤ በአማራ ክልል በ58ሺ804 ተቋማት ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዷል።

ቀጣይ ስራዎች

በድርጊት መርሀ ግብር የተደገፈ ዝርዝር የጋራ ዕቅድ አቅዶ እስከ ወረዳ ድረስ የዋጋ ንረቱን ህገ ወጥና ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ጥረት ማጠናከር፤ በዚህ በጀት ዓመት መሰል የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ከወዲሁ የሰብል ምርቶች እና አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከአምራቹ እስከ ተጠቃሚው ያለውን የግብይት ሰንሰለት ውጤታማ እንዲሆን በጥናት ታግዞ መስራት ይገባል። በዚህም ችግሮችን ከመለየት፤ የመፍትሄ አቅጣጫ ከማመላከትና የመሰረታዊ ሸቀጦችን (የዳቦ ስንዴ፣ ፓልም የምግብ ዘይትና ስኳር) አቅርቦት ሳይቆራረጥ እንዲቀርብ ማስቻል ያስፈልጋል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞች የሚታየውን ሕገ- ወጥ የምርት ክምችት ለማስቀረት ከኦሮሚያ ክልል ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንዲሁም የሕገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ክትትልና ቁጥጥር ስራን በግብር ሃይሉ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል። የህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች ከአጎራባች ክልሎች የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች እንዲሁም ከሃገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቀጥታ በማስተሳሰርና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እንዲቀርብ ማድረግ በትኩረት የሚሰራበት ነው።

ለዚህም በሁሉም ዘርፍ የሚገኙ አምራቾችና አስመጪዎች ባለቤት ሆነው የህዝቡን ችግርና ምሬት ወቅታዊ መፍትሄ ለመስጠት ከመንግስት ጋር በቅንጅት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩና ህብረተሰቡን የሚያማርሩ ህገ ወጦች ላይ አስተማሪ የህግ ማሰከበር ስራ በመስራት በሁሉም ዘርፍ ለዋጋ ንረቱ መንስኤ የሚሆኑ ክፍተቶችን እየለዩ መፍታት ያስፈልጋል።

#EPA

Report Page