#ETH

#ETH


የወላይታ እና የከፋ ዞን አመራሮች የደኢሕዴንን ጥናት አንቀበልም አሉ!

ከታሰበለት ጊዜ ቀድሞ በተጠናቀቀው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ የዞን አመራሮች በክልሉ እየተነሱ ስላሉ የክልልነት ጥያቄዎች ላይ የተካሔደው ጥናት ላይ ውይይት እንዲካሔድ የተቀመጠውን አቅጣጫ የወላይታና የከፋ ዞን አመራሮች በዞናቸው ተግባራዊ እንዳይደረግ መወሰናቸው ታወቀ።

አዲስ ማለዳ ከወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራር አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ባሳለፍነው ሳምንት ለቀረቡለት የክልልነት ጥያቄዎች መፍትሔ ያበጃል ተብሎ የተጠበቀው ምክር ቤቱ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ከታሰበለት ግዜ ቀድሞ መበተኑ በዞን አመራሮቹ ላይ ቅሬታ ፈጥሯል። ለሦስት ቀን ይቆያል በሚል የተጀመረው የምክር ቤቱ ስብሰባ በግማሽ ቀን የመበተኑ ምክንያትም ከዞን ለሚነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ላለመስጠት መሆኑን ገልጸዋል።

የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተከተል ላቤና ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ የክልሉ መንግሥትም ሆነ ደኢሕዴን የእነዚህን ጥያቄዎች ሕገ መንግሥታዊነት እንደሚያከብሩ በተደጋጋሚ የገለጹ ቢሆንም፣ ለአፈጻጸምና ለአስተዳዳር አያመችምና ጥናት ተጠንቶ መፍትሔ ይቀመጥ በማለት ያስቀመጡት ሐሳብ ብዙዎችን ያስማማ ሆኖ አልተገኘም ብለዋል። ለአንዱ ዞን የክልልነት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መብት ሲሰጥ፣ ለሌላው የሚከለክል በመሆኑ የገቡት ቃል ሁልጊዜ ሲከበር አይታይም ሲሉም አክለዋል።

ለውይይት የቀረበውን ሰነድ አስመልክቶ የተዛቡ መረጃዎች ለኅብረተሰቡ በመተላለፋቸው የተፈጠረ ችግር መሆኑን የገለጹት የክልሉ የሚዲያ ሞኒተሪ እና የውጪ ፖሊሲ ሃላፊ ዴያሞ ዳሌ፣ ሰነዱ በድርጅቱ ባህል መሠረት ዝርዝር ጉዳዮች የተፈተሹበትና ችግሮችን አንጥሮ ያወጣ ሲሆን፣ በሰነዱ ላይ የተመላከተው ዝርዝር ግምገማ ያልጣማቸው ግለሰቦች የሚፈጥሩት ውዥንብር ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የደኢሕዴን እና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጌታሁን ጋረደው (ዶ/ር)፣ የክልልነት ጥያቄዎቹ በደኢሕዴን ብቻ የሚመለሱ ስላልሆኑ፣ “እንደ መሪ ፓርቲ ግዴታም ስላለበት ነው ይኼንን ጥናት የሚያደርገው፤” በማለት፣ ጥናቱ ሕገ መንግሥታዊ መንገዶችን ለመጣስ የሚደረግ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ጌታሁን፣ ደኢሕዴን ጥናት የሚያደርገው፣ ደመ ነፍሳዊ የሆነ መለያየት እንዳይሆን ጥንቃቄ የሚያስፈልገውና ከሕዝቦች ጋር ውይይት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ስለሆነ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት የክልሉ ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ላይ የወላይታና የከፋ አመራሮች ጥያቄያቸው በአጀንዳ አለመያዙን አንስተው ሲሞግቱ እንደነበር የአዲስ ማለዳ ምንጮቹ ጠቅሶ ዘግቧል። በሌሎች ዞኖች እስከ ቀበሌ ድረስ ህዝቡን የማወያየት ሥራ እየተሠራ ቢሆንም በወላይታና በከፋ ዞኖች ግን አመራሮቹ ጥያቄውን ባለመቀበላቸው ውይይት አለመጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የሲዳማ ዞን ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረበው የክልልነት ጥያቄ መሠረት ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ፣ በተለያዩ ዞኖች ተመሳሳይ ጥያቄዎች እየተነሱ ሲሆን፣ የዞኖች ምክር ቤቶች ሙሉ በሙሉ በሰጡት የድጋፍ ድምፅ ለክልል ምክር ቤት የክልል እንሁን ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ይከበርልን የሚሉ ጥያቄዎች ተደራርበው መቅረባቸው ይታወሳል።

ምንጭ፦ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ

Report Page