#ETH

#ETH


ሠላምና መረጋጋት እንዲመጣ የፖለቲካ ኃይሎች የሚጋጩ ሕልሞቻቸውን አስቀምጠው ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልጋቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና ፖለቲከኛው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ገለጹ።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ ምሁራን ስለ ሠላም መስበክ፣ ማስተማርና በሚፈጠሩ ቅራኔዎች ላይ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ ለዚህም ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ይነገራል።

ከዘመናዊው ፊዚክስ ሁለት ዓምዶች አንዱ የሆነውን የአንጻራዊነት ንድፈ ሃሳብ ያመነጨው ታላቁ የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን “ሠላምን በኃይል ማስጠበቅ አይቻልም ሠላም ሊጠበቅ የሚችለው በመግባባት ብቻ ነው” ሲል ይገልጻል።

የዓለም ህዝብ ‘እማሆይ ቴሬሳ’ እያለ የሚጠራቸው የካልካታዋ ቅድስት ቴሬሳ ደግሞ “ሠላም የሚጀምረው በፈገግታ ነው” የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው።

ያለ ሁከትና ግርግር የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር እንደሚቻል የሚያምነው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ በበከሉ “ጨለማን በጨለማ ማጥፋት አይቻልም ጨለማን ማስወገድ የሚችለው ብርሃን ብቻ ነው፤ ጥላቻም ጥላቻን አያስወግድም የጥላቻ መድሃኒቱ ፍቅር በመሆኑ ጥላቻን በፍቅር ማሸነፍ ይቻላል” ሲል ተከታዮቹን ለአሉታዊ ነገር ሁሉ አዎንታዊ ምላሽ መስጠትን እንዲያውቁ ያስተምር ነበር።

ሕዝብ ከሁከትና ግርግር ነጻ ሆኖ በወዳጅነት አብሮ ሲኖር ሠላም አለው ይባላል፤ዜጎች ሠላማቸውን ሲያጡ የዋስትና እጦት ውስጥ ይወድቃሉ፣ ህይወታቸው በስጋትና በተስፋ ማጣት ይወጠራል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ ጠና ደዎ ምሁራን የማኅበረሰብ ብልጽግና መሰረት የሆነውን ሠላም ጥቅም ከሁሉም በላይ የሚረዱ በመሆናቸው ስለ ሠላም ማስተማርና ማስገንዘብ እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ።


የሚጠቅምን ከማይጠቅም የሚለዩ ምሁራን ሠላምን ለማጎልበት የድርሻቸውን ለመወጣት ሳያሰልሱ መስራት እንዳለባቸው በማስገንዘብ።

ሠላም ሁለንተናዊ ገጽታ ያለው በመሆኑ ሠላምን ማረጋገጥ የአንድ ወገን ወይም ቡድን ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ተሳትፎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

“ሠላም የሚነሱን ጥቂቶች ናቸው” በማለት የሚገልጹት የፍልስፍና መምህሩ ጥቂቶችን ለማስቆም ብዙሃኑ መተባበር እንደሚኖርበት ነው ያስገነዘቡት።

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ጉልህ ስፍራ ያላቸው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ሠላም ሊረጋገጥ የሚችለው በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት ሲኖር እንደሆነ ይናገራሉ።

“ስብሰባ ስለበዛ ሠላም አይረጋገጥም” የሚል አቋም ያላቸው ፕሮፌሰር መረራ ብሔራዊ መግባባትን የሚያመጣ ተግባር መፈጸም እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።

በተደጋጋሚ በሚካሄዱ ስብሰባዎች የራሱን የሚናገር እንጂ የሌላውን የሚያዳምጥ ተሳታፊ እንደሌለ ጠቁመው

ይህ ደግሞ የሚፈለገውን ሠላም ሊያመጣ እንደማይችል አክለዋል።

መግባባት ሳይኖር የሚወጡ ፖሊሲዎችም ከአንድ ቀውስ ወደሌላ ቀውስ የሚያሸጋግሩ በመሆናቸው ብሔራዊ መግባባት ቅድሚያ ማግኘት ይገባዋል ባይ ናቸው።

ሠላምና መረጋጋት፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና ልማት እንዲመጣ የፖለቲካ ኃይሎች የሚጋጩ ሕልሞቻቸውን አስቀምጠው ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል።

የአገሪቱን ችግር ለመፍታት የፖለቲካ ኃይሎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ፕሮፌሰሩ ይህግን “ኪሳቸው ውስጥ የፖለቲካ ድርጅት ተሸክመው የሚሄዱትን አይመለከትም” ብለዋል።

በሂደቱ መሳተፍ ያለባቸው ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች መሆን እንዳለባቸው በመጠቆም።

ወደስልጣን ለመምጣት የሚደረገውን ጥረት የሰለጠነ ማድረግ ሠላምን እንደሚያረጋግጥ ተናግረው፤ በጉልበት ስልጣን መያዝና ጉልበተኛ ሲመጣ ከስልጣን መውረድ ማብቃት እንዳለበት መክረዋል።

ይህን ሁኔታ የመቀየር ሂደት የተለየ ቀመር የሌለው በመሆኑ የሰለጠነ ፖለቲካ ለማራመድ የፖለቲካ ኃይሎች መወያየትና መተማመን ላይ መድረስእንዳለባቸውም አመልክተዋል።

በሕዝብ ፍላጎት ላይ ያልተመሰረተና ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የሚተገበር አሰራር ቢዘረጋ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ የቀውስ አዙሪት ውስጥ የሚያዳክር በመሆኑ የሕዝብን ፍላጎት ማክበር ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

Via #ENA

Report Page