#ETH

#ETH


በትግራይ ክልል በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ ካሉ መምህራን መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት የሚያስተምሩት ከሰለጠኑበት የሙያ መስክ ውጪ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የመምህራን ምደባው በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር መቆየቱም ተመልክቷል።

ቢሮው የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የክልሉ አጠቃላይ የትምህርት እንቅስቃሴና የ2012 ዕቅድ ላይ አተኩሮ በአክሱም ከተማ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ተጠናቋል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ገብረመስቀል ካህሳይ በመድረኩ ላይ እንዳሉት አሁን በክልሉ ያለው የትምህርት ጥራት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በክልሉ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከተመደቡ መምህራን መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት እያስተማሩ ያሉት በሰለጠኑበት የሙያ መስክ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ይህም በትምህርት ጥራት መጠበቅ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

“ቢሮው ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ መምህራን በሰለጠኑበት ሙያ እንዲያስተምሩ በማድረግ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመፍታት፣ ለትምህርት ጥራት መጠበቅና ለተማሪዎች ብቃት መሻሻል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል” ብለዋል።

በክልሉ በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች የሚመደቡ መምህራን በአዲሱ የትምህርት ዘመን የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው እንዲሆኑ የሚደረግ መሆኑን ኃላፊው ዶክተር ገብረመስቀል ጠቁመዋል።

‘የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ሥራ የአንድ ዓመት ሥራ ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ መምህራን ያለባቸውን ትውልድ የመቅረጽ ሙያዊ ኃላፊነት በማሰብ ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የተማሪዎችን ብቃት የመመዘን፣ የመምህራን ዝግጅት የመከታተል እና የመማር ማስተማር ሂደት ምቹ ማድረግ ላይ የትምህርት አመራሩና ህብረተሰቡ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዶክተር ገብረመስቀል ጥሪ አስተላልፈዋል።

“ከዚህ በፊት የክልሉ ትኩረት በትምህርት ተደራሽነት፣ በተማሪዎች ተሳትፎ እና በትምህርት ግብአት አቅርቦት ላይ ነበር “ያሉት ሃላፊው፣ ዘንድሮ ለጥራትና ለተጠያቂነት አሰራር መስፈን ትኩረት እንደሚሰጥ አስረድተዋል ።

መምህራንና ተማሪዎች ክፍል ጊዜውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለትምህርት ስራ እንዲያውሉ በየጊዜው ክትትል እና ቁጥጥር እንደሚደረገው አመልክተዋል።

“በኮንፈረንሱ ላይ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ እንቅፋት የሆኑ ችግሮች ተለይተዋል፣ በቀጣይ ችግሮቹ እንዳይደገሙ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እንሰራለን” ያሉት ደግሞ የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ርስቁ አለማው ናቸው።

በየደረጃው ያለው የትምህርት አመራር ወደትምህርት ቤቶች በመውረድ በተማሪና መምህራን ላይ ተገቢ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የዓብዪ ዓዲ ከተማ የወላጅ መምህራን ሕብረት አባል አቶ አብርሃ ወልደትንሳኤ በበኩላቸው፣ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ የመምህራን ብቻ ሳይሆን የወላጆችም ጥረት አናሳ መሆኑን ነው የገለጹት።

በቀጣይ ወላጆች የሚጠበቅባቸውን የክትትል እና የቁጥጥር ስራ በአግባቡ እንዲያከናውኑ ጥረት እንደሚደረግም አመልክተዋል።

ለተማሪዎች ውድቀት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት አንዱ ወላጅ የልጁን የትምህርት ሁኔታ አለመከታተሉ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ የወላጆችን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ህብረቱ በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

#ENA

Report Page