#ETH

#ETH


ከጋምቤላ ሆስፒታል የተሰረቀች የአንድ ቀን ተኩል ዕድሜ ያላት ህፃን ከሁለት ቀናት ክትትል በኋላ ከነሙሉ ጤንነቷ ተገኘች ።

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡቲያንግ ኡቻን እንደገለፁት በጋምቤላ ሆስፒታል ነሀሴ 28 ቀን 2011 ዓም አንዲት ህፃን በሰላም ወደ ዓለማችን ተቀላቅላለች ።

ከምጥ ጋር ታግላ ጤናማ ህፃን በሰላም የተገላገለችው እናት ድካሙ አልለቀቃትም ነበርና በማግስቱ አገር አማን ነው ብላ ጨቅላዋን አጠገቧ እንዳስቀመጠች እንቅልፍ ሸለብ ያደርጋታል ።

ከእንቅልፏ ስትነሳ ግን የአንድ ቀን ተኩል እድሜ ያላት የአብራኳን ክፋይ እንዳስቀመጠቻት ከጎኗ የለችም ።

እናት በድንጋጤ ተውጣ የድረሱልኝ ጥሪ በማሰማቷ የሆስፒታሉ ማህበረሰብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ስለ ጉዳዩ ማውረድ ማውጣት ይጀምራል ።

ዋነኛው መፍትሔ ሆኖ የተገኘው ግን ጉዳዩን ለፖሊስ ማሳወቅ ነበር ። የክልሉ ፖሊስም ነሀሴ 29 ቀን 2011 ዓም ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ጠፋች የተባለችውን ጨቅላ ህፃን ለማግኘት ፍለጋውን ይጀምራል ።

የክልሉ ፖሊስ ከሆስፒታሉ ባገኘው የመነሻ ሃሳብ መሰረት በማድረግ ለሁለት ቀናት ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ክትትል ህፃኗ በጋምቤላ ከተማ ቀበሌ 01  ተደብቃ ትናንት ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ በአንድ ግለሰብ ቤት ተገኝታለች ።

ኮሚሽነር ኡቲያንግ እንደገለፁት ህፃኗ ከነሙሉ ጤንነትዋ የተገኘች ሲሆን ፖሊስ ለወላጅ እናቷ አስረክባቷል ።

ጨቅላዋን ሰርቃ ተሰውራለች የተባለችው ተጠርጣሪም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ በምርመራ ላይ ትገኛለች ብለዋል ።

የምርመራ መዘገቡ እንደተጠናቀቀ ተጠርጣሪዋ ለህግ እንደምትቀርብም ከኮሚሽነሩ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

አስገራሚው ነገር ግን እውነተኛዋ አራስም ሆነች በጨቅላ ህፃን ስርቆት ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር የዋለችው ግለሰብ ከሁለት የተለያዩ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የመጡ መሆናቸው ነው ።

አራሷ በጤና ተቋም ለመውለድ ከጀዌ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የመጣችና ከወለደች በኋላም በሀኪሞች ክትትል ላይ የነበረች ስትሆን ህፃኗን የሰረቀችው ደግሞ ከጉኘል የስደተኞች የመጠለያ ጣቢያ የመጣች ናት ተብሏል ።

ለምን እንደመጣችና ህፃኗን ለምን መስረቅ እንደፈለገች በምርመራው የሚታወቅ ይሆናል ተብሏል ።

የጋምቤላ የሆስፒታል ስራ አሰኪያጅ ተወካይ አቶ ኡጃይ ኡበኒ እንዳሉት ሆስፒታሉ ለእናትና ልጅ ተገቢውን ክትትልና የተሟላ የህክምና እንክብካቤ እያደረገላቸው ይገኛል ።

ድርጊቱ በአሮጌው ዓመት ማብቂያ አካባቢ መፈፀሙ ደግሞ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም የሚለውን ብሂል እውነት አስመስሎታል  ።

#ENA

Report Page