#ETH

#ETH


ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ዜጎቹ ጥቃት የተፈጸመባቸው የናይጀሪያ መንግሥት ከደቡብ አፍሪቃ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑ ዜጎቿን ለመውሰድ ማቀዱን አስታወቀ።እቅዱን ይፋ የተደረገው የናይጀሪያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ነው።ናይጀሪያ ዜጎቿ ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት የደቡብ አፍሪቃ አምባሰዷሯን ጠርታለች። ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ በደቡብ አፍሪቃ ዋና ከተማ ፕሪቶርያ እና በንግድ ማዕከሏ በጆሀንስበርግ ከተማ ናይጀሪያውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በውጭ ዜጎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት 5 ሰዎች መገደላቸው፣በርካታ ንብረት መውደሙ እና መዘረፉ ሌሎች ዜጎቻቸው የተጎዱባቸውን የአፍሪቃ ሃገራትንም አስቆጥቷል።ለጥቃቱ የአጸፋ እርምጃ ከተወሰደባቸው ሃገራት ውስጥ ዛምቢያ እና ናይጀሪያ ይገኙበታል።በናይጀሪያ የቴሌኮምኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጠው የደቡብ አፍሪቃው ኩባንያ MTN እና PEP የተባለው የገበያ ድርጅት ጥቃት ከደረሰባቸው የደቡብ አፍሪቃ ድርጅቶች ውስጥ ይገኙበታል። ከጥቃቱ በኋላም ናይጀሪያ የሚገኙ የደቡብ አፍሪቃ የንግድ ድርጅቶች ተዘግተው በፖሊስ እየተጠበቁ ነው።ትናንት ዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች አደባባይ በመውጣት ተቃውሞአቸውን አስምተው ነበር።ተማሪዎቹ በዚያ የሚገኙ የደቡብ አፍሪቃ የንግድ ድርጅቶችን የማጥቃት እና የመዝረፍ ሙከራ ማድረጋቸውም ተዘግቧል። ደቡብ አፍሪቃም ባደረባት ስጋት እና ለሠራተኞቼ ደህንነት ስትል ሌጎስ ናይጀሪያ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለጊዜው መዝጋትዋን ዛሬ አስታውቃለች።ቦትስዋና ዜጎቿ በደቡብ አፍሪቃ ሲንቀሳቀሱ ልዩ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ሁኔታዎችን በንቃት እንዲከታተሉ አሳስባለች።ዘረኛውን ጥቃት የአፍሪቃ ህብረት ፣የናይጀሪያው ፕሬዝዳንት ሙሀማዱ ቡሃሪ እና የደቡብ አፍሪቃው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳም አውግዘዋል።ሁከቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶተጠርጣሪ 300 ሰዎች ታስረዋል።

Via #DW

Report Page