#ETH

#ETH


የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነታሪኩ ለማ ላይ የዋስትና እግዱን አጸና

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኃላፊዎችን ጨምሮ በዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ላይ የቀረበው የዋስትና እግድ እንዲጸና ወሰነ። የስር ፍርድ ቤት ለተጠርጣሪዎቹ የፈቀደውን የ50 ሺህ ብር ዋስትና እንዲታገድ የጠየቀው ጉዳያቸውን እየመረመረ የሚገኘው ፖሊስ ነው።

በሐዋሳ ከተማ እና በሲዳማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች እጃቸው አለበት በሚል በእስር ላይ የሚገኙ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎችን ዋስትና ፈቅዶ የነበረው የሀዋሳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነበር። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል የዋስትና መብትን የሚከለክል ከመሆኑም በላይ «በዋስ ከወጡ መረጃዎችን ሊያጠፉ፣ ምስክሮችን ሊያባብሉ ይችላሉ» በማለት ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የእግድ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወቃል።

ይግባኙ የቀረበለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበትን ወንጀል በስር ፍርድ ቤት ከተፈቀደው የዋስትና መብት አንጻር ካገናዘበ እና እስካሁን ለመርማሪ ፖሊስ የተሰጠው የምርመራ ጊዜ በቂ መሆን ወይም አለመሆኑን ከመረመረ በኋላ ዛሬ ውሳኔ ሰጥቷል። የዛሬውን የችሎት ውሎ እንዲከታተሉ ከተፈቀደላቸው የተጠርጣሪ ቤተሰቦች መካከል የሆኑት የወይንእሸት ገናሌ እና ለምለም ለማ ለዶቼ ቨለ (DW) እንዳሉት ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን የይግባኝ መቃወሚያ በማፅናት ቀደም ሲል በበታች ፍርድ ቤት የተፈቀደውን የዋስትና መብት ሽሮታል።

የተጠርጣሪዎች መዝገብም ወደ ሀዋሳ ከተማ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተመልሶ የችሎት ሂደቱ ካቆመበት እንዲቀጥል መወሰኑን ገልጸዋል። ዘጠኙ ተጠርጣሪዎች ከ14 ቀናት በኋላ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱን የተጠርጣሪ ቤተሰቦች ገልጸዋል። ዛሬ ፍርድ ቤት ከቀረቡት ውስጥ ተጠርጣሪዎቹ የሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጌታሁን ደጉዬ፣ ምክትላቸው ታሪኩ ለማ እና የዚሁ ጣቢያ የቦርድ አባል የሆኑት በላይ ባልጉዳ ይገኙበታል።

በከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ የተከናወነው የዛሬው የፍርድ ቤት ሂደት ለጋዜጠኞች ዝግ ነበር። የችሎቱን ሂደት ለመዘገብ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኙ የመንግሥት እና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች «ከሚመለከተው አካል ልዩ የድጋፍ ደብዳቤ ካላመጣችሁ በችሎቱ መታደም አትችሉም» በመባላቸው ወደ ግቢው ሳይገቡ ከበር ለመመለስ ተገደዋል። ወደ ችሎት አዳራሽ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ጥቂት የተከሳሽ የቅርብ ዘመዶች ብቻ ነበሩ።

በሀዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ባለፈው የሐምሌ ወር አጋማሽ የሲዳማ ክልል እንዲታወጅ የሚጠይቁ ወጣቶች ከጸጥታ ሀይል አባላት ጋር መጋጨታቸውን ተከትሎ በትንሹ 53 ሰዎች ሲሞቱ፣ ሌሎች 54 ደግሞ መቁሰላቸውን እና በሚሊዮኖች ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የሲዳማ ዞን ፖሊስ መምሪያ ማስታወቁ አይዘነጋም። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በሕግ የተጠረጠሩ 935 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ ገልጾ ነበር።

#DW

Report Page