#ETH

#ETH


የቀድሞው ማዕከላዊ እስር ቤት ለጉብኝት ክፍት እንደሚደረግ ተገለጸ!

ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበረውን የፍትህ ቀን ምክንያት በማድረግ የቀድሞው ማዕከላዊ እስር ቤት ለጉብኝት ለህዝብ ክፍት እንደሚደረግ የበአሉ የኮሚዩኒኬሽን፣ሚድያና መድረክ ዝግጅት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዝናቡ ቱኑ ገለጹ፡፡

እስር ቤቱ ከዚህ ቀደም በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸምበት እንደነበር የሚታወስ ሆኖ ለውጡን ምክንያት በማድረግ መንግስት እንዲዘጋና ወደ ሙዚምነት እንዲቀር መወሰኑ ይታወቃል፡፡ በማእከላዊ እስር ቤት በፖለቲካ ነክ የህግ ተጠያቂ እስረኞች ላይ የማይሻር የስነ-ልቦና ቅጣት እስከ አካል ማጉደል የሚያደርስ የስቃይ ዘዴዎች ይፈጸሙ ነበር፡፡

በተጨማሪም በተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራ ሂደት ሲከናወን በጨለማ ቤቶች ተዘግተው ከፍተኛ የሆነ ጫናና በደል ሲደርስባቸው አንዳንዶችም ህወታቸው ያልፍ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ሆኖ የእናቶች እንባ ከታበሰና የለውጡ ምህዳር ከሰፋ ጊዜ ጀምሮ እስር ቤቱ ዝግ ተደርጎ በዚህ ቦታ ላይ ይፈጸም የነበረው የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብት ጥሰት ቆሟል፡፡

ኮሚቴው እንዳስታወቀው የፍትህ ቀንን ምክኒያት በማድረግ እስርቤቱ ለጉብኝት ከጳጉሜን 1 እስከ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ለሁሉም ሰው ክፍት ሆኖ እንደሚቆይና በህብረተሰቡ ጉብኝት እንደሚደረግ በተጨማሪም በየፍትህ አካላት ማለትም በጠቅላይ ፍርድ ቤት፣በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የተለያዩ የስዕል አውደ ርዕዮች እና በፍትህ ላይ የሚያጠነጥኑ የኤግዚቢሽን መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል።

እስር ቤቱ በአገልግሎት ላይ እያለ ተጠርጣሪዎች የሚመረመሩባቸውን ጨለማ ቤቶች ከጳጉሜ1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 4 ቀናት ለዕይታ ለህዝብ ክፍት ስለሚደረግ ማንኛውም ህብረተሰብ በተገለጹት ቀናቶች በቦታው ላይ በመገኘት የጉብኝት መርሃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ኮሚቴው ጥሪ ማስተላለፉን ከጠቅላይ አቃቤ ህግ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Via #EPA

Report Page