#ETH

#ETH


በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ኃይል በየመን በፈጸመው የአየር ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታወቀ።

ቀይ መስቀል እንዳለው ከሆነ በተደጋጋሚ በተፈጸመው የአየር ጥቃት የተገደሉት በእስር ቤት ውስጥ ታጉረው የነበሩ ሰዎች ናቸው።

ከአየር ጥቃቱ በህይወት መትረፍ የቻሉ 40 ሰዎች ህክምና እየተደረገላቸው በመሆኑም ተነግሯል። የአየር ጥቃቱ ቢያንስ ስድስት ጊዜ መፈጸሙን ከአየር ጥቃቱ የተረፉት እና በአከባቢው የሚኖሩ ሰዎች ተናግረዋል።

በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ኃይል የየመን መንግሥትን የሚደግፍ ሲሆን፤ የሰነዘርኩት ጥቃት የድሮን እና የሚሳዔል ይዞታዎችን አውድሟል ብሏል።

በኢራን የሚደገፈው የሁቲ አማጺያን ቡድን በበኩሉ የሳዑዲው ጥምር ኃይል ጥቃት ያደረሰው እንደ እስር ቤት በምጠቀምበት ይዞታ ላይ ነው ብሏል።

የቀይ መስቀል ተወካይ የሆኑት ፍራንዝ ራኤቸስታይን በአየር ጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመታደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጽዋል።

እ.አ.አ. 2015 ላይ የየመን ፕሬዝደንት አብደራቡህ ማንሱር ሃዲ በሁቲ አማጽያን ከመዲናዋ ሰነዓ ተባረው እንዲወጡ ከተደረገ ጀምሮ የመን ማለቂያ የሌለው ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።

ሳዑዲ አረቢያ በቀጠናው የሚገኙ ሌሎች ሃገራትን በማስተባበር ለፕሬዝደንት አብደራቡህ ማንሱር ሃዲ ድጋፍ እያደረገች ሲሆን፤ ኢራን ደግሞ ለሁቲ አማጽያን ድጋፍ ታደርጋለች።

በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ኃይል የሁቲ አማጽያን ላይ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት የሚፈጽም ሲሆን የሁቲ አማጽያንም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሮኬቶችን ያስወነጭፋሉ።

ይህ ጦርነት ወደ 24 ሚሊዮን የሚጠጉ የመናውያን አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂዎች እንዲሆኑ ያደረገ ሲሆን፤ በእርስ በእርስ ጦርነቱ ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ ከ70ሺህ በላይ ሰዎች ስለመገደላቸው የተባበሩት መንግሥታት አሀዞች ይጠቁማሉ።

VIA #BBC

Report Page