#ETH

#ETH


ለኢትዮጰያ ጠንካራ አንድነት፣ ሰላምና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት አበክሮ እንደሚሰራ የኢትዮጰያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ገለፀ ።

ኢዜማ ከደሴና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር በለውጡና በቀጣይ የሰራ እቅዶቹ ዙሪያ ትናንት መክሯል፡፡

የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ የአገሩን ዳር ድንበር አስከብሮ፣ ተከባብሮና ተቻችሉ ክፉ ደጉን አሳልፏል፡፡

ይህን ከአባቶች የተገኘውን የረጅም ዘመን አንድነት፣ ሰላምና የመቻቻል ባህልና እሴት ለማጎልበት ኢዜማ አበክሮ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ከተደቀነባት አደጋ ለማውጣት በየደረጃው ጠንካራ መሪና ህዝብ ያስፈልጋታል ያሉት አቶ አንዷለም ከዚህ ችግር እንድትወጣ ከመንግስትና ከሌሎች ተፎካካሪ ፓሪቲዎች ጋር ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አንዷለም ገለጻ ከማንኛዉም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በፊት አገር ፣ አንድነትና ሰላም መቅደም እንዳለበትም አብራርተዋል፡፡

ወጣቱ ማንኛዉንም ተፎካካሪ ፓርቲ ሲደግፍና ሲቃወም በምክንያት መሆን አለበት የሚሉት አቶ አንዷለም የኢትዮጵያ ድንቅ ታሪክ ፣ ወግና ባህል እንዲከበርም ፓርቲዉ ይሰራል ፡፡

የፓርቲዉ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ በበኩላቸዉ በኢትዮጵያ በየትኛዉም ቦታ ማንኛዉም ሰዉ ያለ ስጋት ሰርቶ የሚኖርባት ሀገር ለመፍጠር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ጫፍ የደረሰዉን ዘረኝነትና ጎጠኝነት በመዋጋት ዘላቂ ሰላምና ዲሞክራሲ፣ እኩል የሐብት ክፍፍልና ፍትሃዊነት እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥም ፓርቲዉ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“ጦር ከፈታዉ ወሬ የፈታዉ” እንደሚባለዉ በዘርና በሐይማኖት ከፋፍለዉ በሐሰት መረጃ ኢትዮጵያን ለማፈራረሰ የሚጥሩ ጥቅም ፈላጊ ዘረኛ ፖለቲካኞችን በጋራ መዋጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ አተኩረን ተቻችለንና ተከባብረን በውይይት ችግሮችን መፍታት አማራጭ የሌለው መፍትሄ በመሆኑ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አህመድ መኮነን በሰጡት አስተያየት ወጣቱ ትውልድ ያጠፋውን በመምከር ፣ በፍቅርና በይቅርታ አልፎ የአባቶችን ታሪክ መድገም ይጠበቅበታል፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከራሳቸዉ ጥቅም ይልቅ አገርና ህዝብን በማሰቀደም ለሰላምና ለአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የተፎካካሪ ፓርቲዎች መብዛት ጥሩና መጥፎዉን፤ ዉሸታምና እዉነተኛዉን ለመለየት ተቸግረናል ያሉት አቶ አህመድ ማንኛዉም ፓርቲ የማይፈጽመዉን ቃል መግባት የለበትም ብለዋል፡፡

በወሎ ባህል አምባ አዳራሽ በተደረገዉ ዉይይት ከደሴ ከተማና አካባቢዋ የተዉጣጡ ነዋሪዎች፣ የፓርቲዉ ደጋፊዎች፣ አባላትና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡

#ENA

Report Page