#ETH

#ETH


” እራሳችንን ጠቅመን አገራችንና ህዝባችንን ለማገልገል የገነባናቸው ፋብሪካዎች በኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ምክንያት ወደ ማምረት ተግባር መግባት አልቻሉም ” ሲሉ በደሴ ከተማ የሚገኙ ባለሃብቶች ቅሬታ አሰሙ ።

” በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደሴ ዲስትሪክት በበኩሉ በአሁኑ ጊዜ የሃይል እጥረት በማጋጠሙ ችግሩ ከአቅሜ በላይ ነው ብሏል ።

አቶ ሁሴን አህመድ በደሴ ከተማ ገራዶ አካባቢ በ21 ሚሊዮን ብር የዱቄትና መኮረኒ ፋብሪካ ገንበተዉ ካጠናቀቁ አንድ ዓመት ቢያልፋቸውም በኤሌክትሪክ አገልግሎት ማጣት ምክንያት ወደ ማምረት ስራ መግባት እንዳልቻሉ ገልፀዋል ።

ለትራንስፎርመር ብቻ 800 ሺህ ብር ከከፈሉ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው የተናገሩት ባለሃብቱ እስከ አሁን ድረስ ምላሽ ባለማግኘታቸው በቀን 620 ኩንታል ዱቄት ማምረት የሚችልና ለ78 ወገኖች የስራ እድል የሚፈጥረው ፋብሪካ ያለአገልግሎት መቆሙ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል ።

ከልማት ባንክ የተበደርነውን ገንዘብ ሳንሰራበት እየወለደ ለኪሳራ ከመክሰራችን በፊት መንግስት አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሊታደገን ይገባል” ብለዋል፡፡

ሌላው የጢጣ ፕላስቲክና ከረጢት ማምረቻ ፋብሪካ ሥራ አስካሄጅ አቶ አንተነህ አማረ በበኩላቸው በ60 ሚሊዮን ብር የገነቡት ፋብሪካ በኤሌክትሪክ አገልግሎት ማጣት ሳቢያ ስራ ባለመጀመሩ ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

ትራንስፎርመር ለማስገባት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ከፍለው ከአንድ ዓመት በላይ ቢጠባበቁም አገልግሎቱ ማግኘት እንዳልቻሉ አስረድተዋል ።

ፋብሪካው በ2011 ዓ.ም ወደ ማምረት በማሸጋገር 17 ሚሊዮን ከረጢቶችን ለማምረትና ከ300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት አለመሳካቱን ተናግረዋል ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ በላይነህ ኃይሉ ስለ ጉዳዩ በሰጡት አስተያየት በኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚደርሰውን ችግር ሌሎች ባለሃብቶች ወደ አካባቢው እንዳይመጡ ተፅእኖ እያሳደረ ነው ብለዋል ።

በግንባታ ላይ ያሉ ባለሃብቶች ተስፋ እንዲቆርጡ ከማድረጉም በላይ በከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ በመነሳቱ ከዲስትሪክቱ ጋር ተደጋሚ ውይይት ቢደረግም መፍትሄ እንዳልተገኘለት የመምሪያ ኃላፊው ገልፀዋል ።

ከ35 በላይ የሚሆኑ ሆቴሎችና አነስተኛ ድርጅቶችም በመብራት ችግር ምክንያት መጉላላታቸውን አቶ በላይነህ ተናግረዋል ።

በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደሴ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሀብቱ አበበ በችግሩ ዙሪያ ተጠይቀው በአካባቢው የሀይል አቅርቦት ችግር በመኖሩ ለፋብሪካዎች ቀርቶ ለመኖሪያ ቤትም አዲስ ደንበኞች ተቀብለን አገልግሎት መስጠት አልቻልንም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ።

ችግሩ ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የክልልና የፌደራል አካላት አሳውቀን መልስ እየተጠባበቅን እንገኛለን ብለዋል፡፡

#ENA

Report Page