#ETH

#ETH


ቅዱስ ሲኖዶስ የኦሮሚያ ቤተክህነት ፅህፈት ቤት ጥያቄን በ30 ቀናት እንዲመልስ ቀነ ገደብ ተቀመጠ!

የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት በክልል ደረጃ እንዲዋቀር የቀረበው ጥያቄ ምላሽ ቅዱስ ሲኖዶሱ በ30 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቃቸው ይህ ተግባራዊ ካልሆነ ግን አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ በላይ መኮንን አስታውቀዋል።

በዛሬው ዕለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ኮሚቴው ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ክልላዊ ፅህፈት ቤቱን ጥያቄ የሚቀበለው ከሆነ የሰው ኃይል አመዳደቡም ሆነ አፈፃፀሙ ይህ አደራጅ ኮሚቴና ጠቅላይ ቤተ ክህነት በጋራ የሚወስኑት እንደሚሆን ተገልጿል።

በተጠየቀው መሰረት አስቸኳይ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ የምዕመኑን ጥያቄ ለመመለስ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ኮሚቴው አስጠንቅቋል። እርምጃው ምን እንደሆነ በዚህ ወቅት ግልፅ ባያደርጉም ከዚህ ቀደም እንደተናገሩት በራሳቸው ክልላዊ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት እናቋቁማለን ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ቀሲስ በላይ በዚህ ወቅት እንደገለፁት ጉባኤው እምነቱ አንድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ አንድ ፓትርያርክና አንዲት ቤተ ክርስቲያን መሆኑን አምነው የቤተ ክርስቲያኗን ሌላ ህግ ማውጣት እንደማያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ክልላዊ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት የማቋቋም ጥያቄ የቤተ ክርስቲያኗ የዶግማና የቀኖና ትውፊት ለውጥ ሳይኖር አስተዳደራዊ ችግሮችን ለመፍታት መዋቅር የማበጀት ጥያቄ መሆኑንም ገልፀዋል።

ጥያቄው አዲስ እንዳልሆነና ታሪካዊ ዳራ ያለው መሆኑን ተናግረው ቤተክርስቲያኗ በአፄ ኃይለ ስላሴ አገዛዝም ወቅት በጠቅላይ ግዛት በአውራጃና በወረዳ ደረጃ የመንግሥት አደረጃጀት ተከትላ ትሰራ እንደነበርና እንዲሁም በደርግ ወቅትም ይህ አሰራር እንደቀጠለ ገልፀዋል።

በኢህአዴግ አገዛዝም ወቅት የፌደራል አደረጃጀቱን ተከትሎ ኃገረ ስብከቶች መቋማቸውንና በክልል ደረጃ ፅህፈት ቤት ማጣቷ ላለው ማህበረሰብ ተደራሽነት ሳይኖረው እንደቀረ ተናግረዋል።

"በክልል ደረጃ መብቷን የሚያስከብርላት የለም" ብለዋል።

ቀሲስ በላይ አክለውም ቤተ ክርስቲያኗ በልዩ ልዩ ቋንቋና ለተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ለመደረስ መዋቅር መዘርጋት ከአንድነቷ ጋር የማይፃረር ነው ብለዋል።

ከአስተዳደራዊ ችግሮችም ጋር በተያያዘ የተደራሽነቷ መጠን መቀነሱን ተናግረው የቤተ ክርስቲያኗ ምዕመናን መኮብለላቸውን፣ አብያተ ክርስቲያናት በከፍተኛ ቁጥር የቀነሰ ሲሆን ይህም በከፍተኛ የሚስተዋልበት የኦሮሚያ ክልል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።

የኦሮምኛ ቋንቋ በክልሉም ሆነ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል ቢነገርም ቤተ ክርስቲያኗ ያሏት ጥቂት ዲያቆናት፣ አገልጋዮችና መምህራን ብቻ በመኖራቸው እነዚህም ለአዲሱ ትውልድን ያማከለ ቋንቋ የሚናገሩ ባለመሆኑ ክልላዊ መዋቅሩ መፍትሄ ሊያበጅለት ይችላል ብለዋል። ይህ ችግር ሁሉንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችን የሚመለከት መሆኑንም አስምረዋል።

በክልሉ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት እንዲቋቋም በተደጋጋሚ ለቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስና ለቅዱስ ሲኖዶሱ የቀረበ ሲሆን አስፈላጊነቱ ቢታመንም ምላሽ እንዳላገኘ ገልፀዋል።

በአቡነ ማትያስ የፓትርያርክነት ዘመንም የክልሉ አባገዳዎችና ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶሱ በ2010 ዓ.ም ጥያቄው ቢቀርብም እሰስካሁን ምላሽ እንዳልተገኘ ተናግረዋል።

"አላማው ምድራዊ ፖለቲካ፣ ቁሳዊ ፍላጎትን በቤተ ክርስቲያን ላይ ለመጫን አይደለም። ዋናው አላማ ቤተክርስቲያኗ ሁሉም በእኩልነት የሚገለገልባት እንድትሆን ነው፤ አድሎንም እንጠየፋለን" ብለዋል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቤተ ክህነት በኦሮሚያ ቤተክህነት ፅህፈት ቤት አደራጅ ኮሚቴ የተጠራውን መግለጫ እንደማያውቀውና እውቅናም እንዳልሰጠው የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ስራ አስኪያጅ ርዕሰ ደብር መሀሪ ኃይሉ በትናንትናው እለት መግለፃቸው የሚታወስ ነው።

Via #BBCAMHARIC

Report Page