#ETH

#ETH


በጅግጅጋ ከተማ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 29ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ በዛሬው እለት ተጠናቋል።

ጉባኤው በቆይታው የ2011 አም የእቅድ አፈፃፀም እና የ2012 እቅድ ላይ የመከረ ሲሆን፥ በሶስተኛው ቀን ውሎም አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ላይ መክሯል።

በዚሁ ፍኖተ ካርታ ላይም በአመዛኙ አተገባበሩ ላይ ቢስተካከሉ እና እንደገና ቢታዩ ያሏቸውን ነጥቦች አንስተዋል ጉባኤተኛቹ።

በዚህም ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር የሽግግር ጊዜና ከቀደመው ስርአት መውጫ ስትራቴጅ ያስፈልጋል፣ለመምህራን የተሰጠው ስልጠና በቂ አይደለም፣ የመፅሀፍ እና ትምህርት ግብአት ዝግጅት በበቂ ሁኔታ አልተሟላም፣ ሁሉም ሳይስማማበት ወደ ትግበራ መግባቱ ችግር ይፈጥራል፣ ያልተወያዩ ክልሎችና የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ፣ የሚሉ ሃሳቦች ተነስተዋል።

በተጨማሪም ጉባኤተኛው በፍኖተ ካርታው የክልልና የፌዴራል ሃላፊነት በግልፅ አልተቀመጠም፣በምን መልኩ እንደሚተገበር ግልፅ አልሆነም፣ መምህራን በተመለከተ የተቀመጠው በስራ ላይ ያሉትን ያላገናዘበ ነው፣ ለአርብቶ አደሮች ልዩ ስትራቴጅ ይዘጋጅላቸዋል የሚለው በግልፅ አልተቀመጠም፣ የሚሉ ነጥቦችንም አንሰረተዋል።

ከዚህ ባለፈም የ8ተኛ ክፍል ፍኖተካርታው ሲተገበር የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች እጣ ፋንታ ምን ይሆናል፣ የ8ተኛ ብሄራዊ ፈተናን የሚያዘጋጀው ማን ነው የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል በተሳታፊዎቹ።

ብሄራዊ የስራ ቋንቋን ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ጋር በዝቅተኛ የክፍል ደረጃ መሰጠት እንዲጀመር የተቀመጠው ሃሳብም በስፋት አከራክሯል።

በአንዴ ከመጫን ይልቅ ደረጃ በደረጃ ቢተገበር፣ ፍኖተ ካርታውን በተመለከተ በሁሉም ዘንድ ተመሳሳይ አቋም ቢያዝ፣ ከመተግበሩ በፊትም የፓሊሲ መከለስ ስራው ቢቀድም፣ በህግ መታየት ያለባቸውም በቶሎ ምላሽ ያግኙ የሚሉት በምክረ ሃሳብነት የቀረቡ ናቸው።

የዝግጅት አመቱ እና መውጫ ስትራቴጅው አስፈላጊ መሆኑን አንስተው የመተግበሪያው አመት 2013 እንደሚሆንና፣ 2012 ቀሪ የማጠናቀቂያ እና የዝግጅት አመት ይሆናል ብለዋል።

በዚህም የ8ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በ2013 እንደሚጀመርና የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ይሰጣል፣ ወደ 11ኛ ክፍል የሚያልፉ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን ቁጥር በተመለከተ ተወያይተን እንወስናለን ብለዋል።

ከክፍል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ተለዋዋጭ እንደሚሆን ያነሱት ዶክተር ጥላዬ፥ በአምስት አመት ውስጥ ከቀደመው ስርአት የመውጣት ሃሳብ እንዳለ ጠቁመዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትም ውክልና ካልተሰጠው በስተቀር የክልሎች መሆኑን ያነሱት ዶክተር ጥላዬ፣ የ8ተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን በተመለከተ የፌደራል መንግስት ስታንዳርድ የማውጣት ሚና እንጅ የመፈተን አይሆንም ይልቁንም ፈታኞቹ ክልሎቹ ናቸው ብለዋል።

የአማርኛ ቋንቋ ከአንደኛ ክፍል ይጀምራል የሚለው፣ በክልሎቹ እንደሚወሰን ያነሱት ዶክተር ጥላዬ፣ ቋንቋን በተመለከተ በፍኖተ ካርታው የተቀመጠው የአፍ መፍቻ ቋንቋን ወደኋላ የሚመልስ ሳይሆን እስከ ሶስተኛ ዲግሪ እና የማስተማሪያ ቋንቋ የማድረግ ግብ ያለው ብዝሃ ቋንቋ ተናጋሪነትንም የሚያበረታታ ነው ብለዋል።

በፍኖተ ካርታው ከተቀመጡት የነፃ የትምህርት እድል፣ የግዴታ ትምህርት፣ ወጭ መጋራት እና የብሄራዊ አገልግሎትና በጎ ፈቃድ በአዋጅ እና በህግ ምላሽ ማግኘት ያለባቸው የትምህርት ህጉ ጉዳዬች ናቸው ብለዋል።

የፓሊሲ ክለሳ ስራው እየተሰራ ነው፤ ጎን ለጎንም ፍኖተ ካርታውን ለመተግበር ጥረት ይደረጋል ፍኖተ ካርታው ከየት ወዴት የሚለውን የሚያሳይ እንጅ በራሱ እቅድ አይደለም፣ህዝቡ የተማረረባው የትምህርት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ስለሚቀድም፣ስለሆነም ሁሉንም በጊዜ የለንም መንፈስ ለመተግበር መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በመጨረሻም ጉባኤተኛው ፍኖተ ካርታውን ለመተግበርና ብቁ ዜጋን የማፍራት ስራቸውንእንዲሁም የተያዙ እቅዶችን ለማሳክት ለመስራት ተስማምቷል።ጉባኤውም ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ የ30ኛው የትምህርት ጉባኤ አስተናጋጅ ጋምቤላ መሆኑ ታውቋል።

#FBC

Report Page