#eth

#eth


በጋምቤላ ፈቃድ የሌላቸው 11 የውጭ ኮሌጆች ተገኙ!

ከየት እንደመጡ ያልታወቁ 11 ሕገወጥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጋምቤላ ክልል ሲያስተምሩ እንደተደረሰባቸው፣ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ከተለያዩ ግለሰቦች በደረሰው ጥቆማ መሠረት ወደ ክልሉ ተንቀሳቅሶ የለያቸው እነዚህ 11 ተቋማት በድኅረ ምረቃና በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ተማሪዎችን እየተቀበሉ እንደሚያስተምሩ ለሪፖርተር የገለጹት፣ የኤጀንሲው የኮሙዩኔኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ገረሱ ናቸው፡፡

ከኤጀንሲው ፈቃድ ሳያገኙ ሊያስተምሩ የተገኙት 11 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በአገር ውስጥ የማይታወቁና እንግዳ መጠሪያ ያላቸውና ከውጭ የገቡ እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹በተደጋጋሚ በደረሰን ጥቆማ መሠረት ለማጣራት ወደ ክልሉ ስናመራ የጠበቅነው አንድ ተቋም ብቻ ነበር፡፡ ስንደርስ ግን 11 ሆነው አገኘናቸው፡፡ በወቅቱ ምንም ማድረግ ስላልቻልን ለክልሉ መንግሥት ስለሁኔታው በማስረዳት የክልሉን ነዋሪዎች ከሕገወጦች እንዲጠብቅ ደብዳቤ ጻፍን፤›› የሚሉት አቶ ታረቀኝ፣ ለክልሉ ደብዳቤ ከተጻፈ ስድስት ወራት የተቆጠረ ቢሆንም ምንም ዓይነት ምላሽ ለኤጀንሲው አለመድረሱን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ ክልሉ ውስጥ ገብተው ሲያስተምሩ ምን ያህል ጊዜያት ማስቆጠራቸውን፣ እስካሁን ምን ያህል ተማሪዎችን ማስመረቃቸውንና እያስተማሩ መሆናቸውን በውል እንደማይታወቅ፣ በቀጣይ በሚደረግ ማጣራት ይፋ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩ ከምን እንደደረሰም በቅርቡ ወደ ክልሉ ተንቀሳቅሰው ማጣራት እንደሚደረግም አክለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ 2011 ዓ.ም. ኤጀንሲው በተቋማት አሠራር ላይ ከፍተኛ ክትትል ያደረገበት ዓመት ነው ያሉት አቶ ታረቀኝ፣ በበጀት ዓመቱ 18 ካምፓሶች እንደተዘጉ ገልጸዋል፡፡ የተዘጉት ካምፓሶች በአዲስ አበባና ዙሪያዋ፣ በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች የዕውቅና ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲያስተምሩ የተገኙ እንደሆኑም አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ኤጀንሲው በነበረው የአሠራር ችግር አስፈላጊውን ቁጥጥርና ፍተሻ ማድረግ ላይ ክፍተት እንደነበረበት፣ የዕውቅና ፈቃድ ለመስጠት እንኳ እስከ ሁለት ዓመት ጊዜ የሚፈጅበት ሁኔታ እንደነበር የገለጹት አቶ ታረቀኝ፣ የነበረበትን ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ፈቃድ ባላገኙባቸው ፕሮግራሞችና ካምፓሶች ተማሪዎችን እየተቀበሉ የሚያስተምሩ ብዙ ተቋማት እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በየተቋማቱ የሚማሩ የተማሪዎች ቁጥር ለኤጀንሲው በአግበቡ አይደርሰውም፡፡ የመማሪያ ክፍሎች፣ የላይብረሪ አደረጃጀት፣ የመምህራን ቁጥር ላይ ተመሥርቶ ኤጀንሲው ከሚፈቅደው የተማሪዎች ቁጥር በብዙ እጥፍ ጨምረው ይቀበላሉ ብለዋል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተቋሙ በነበረው መረጃ 88 ሺሕ ተማሪዎች በግል የትምህርት ተቋማት የሚማሩ ቢሆንም፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባደረገው ማጣራት ግን 202 ሺሕ ተማሪዎች መኖራቸው ተረጋግጧል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ለእኛ እንዲህ ቀንሰው ከነገሩን ለገቢዎች ሚኒስቴር በምን ያህል መጠን ቀንሰው ሊነግሩ እንደሚችሉ እንግዲህ ማሰብ ነው፤›› ያሉት አቶ ታረቀኝ፣ የመምህራን ቁጥራቸውን ሳይቀር የሚያጭበረብሩ የትምህርት ተቋማት መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የችርቻሮ፣ የጋራዥ፣ የአስመጪና ላኪ ፈቃድ አውጥተው ከኤጀንሲው ዕውቅና ሳያገኙ የሚያስተምሩ ጥቂት የማይባሉ ኮሌጆች እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡

ገበያ ለመሳብ ሲሉ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ደረጃ ላይ ያልደረሱ ተቋማት ራሳቸውን ዩኒቨርሲቲ እያሉ እንደሚያስተዋውቁ፣ እንዲህ የሚያደርጉ ተቋማትም ስያሜያቸውን በደረጃቸው ልክ እንዲያስተካክሉና ማስታወቂያ የሚሠሩ የሚዲያ ተቋማትም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ኤጀንሲው ለሪፖርተር በላከው ሰነድ መሠረት በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ 198 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አራት ዩኒቨርሲቲዎች፣ አምስት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች፣ አሥር ኢንስቲትዩቶች፣ የተቀሩት በሙሉ ደግሞ ኮሌጆች ናቸው፡፡

#ሪፖርተር_ጋዜጣ


Report Page