#ETH

#ETH


ትዴት የአማራ እና ትግራይ ወጣቶች የወዳጅነት መድረክ ሊያዘጋጅ ነው!

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) «ቀጣይ ትውልድ» በሚል መሪ ቃል የአማራና ትግራይ ክልል ወጣቶች የሚሳተፉበት የወዳጅነት መድረክ በባህር ዳር፣ ቆቦ፣ አላማጣ፣ አዲስ አበባ እና መቀሌ ከተሞች በመስከረም 2012 መካሄድ እንደሚጀመር አስታወቀ።

የትዴት ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉ ብርሃን ኃይለ፣ ዝግጅቱን በቀጣዩ መስከረም ወር ላይ ለመጀመር ፈቃደኛ ከሆኑ ግለሰቦች ገንዘብ ማሰባሰብ መጀመራቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸው፣ የትዴት ድጋፍ እንዳለ ሆኖ ከአማራ ክልል መንግስትም የገንዘብ ድጋፍ መጠየቃቸውን አውስተዋል።

የፓርቲው የትዴት ምክትል ሊቀመንበር ግደይ ዘርዐጽዮን ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በሁለቱ ክልሎች አመራሮች መካከል የሚታየው ሽኩቻ ወደ ወጣቱ አምርቶ ሌላ ችግር ከማምጣቱ በፊት፣ የሁለቱ ክልል ወጣቶች መክረውና ተወያይተው ችግሮቻቸውን መፍታት ይችላሉ፣ በሚል ዝግጅቱን ለማከናወን መታሰቡን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ፓርቲው መድረኩን ከማዘጋጀት ባለፈ ሌላ ሚና አይኖረውም፣ ከማንም ጣልቃ ገብነት ነጻ በሆነ መልኩ በሁለቱ ክልል ወጣቶች ብቻ የሚከናወን ይሆናል። ያለአግባብ የሆኑ እንቅስቃሴዎች ተቀርፈው ታሪካዊ ወዳጅነት እንዲፈጠርና አብሮ የመሥራት ተሞክሮ እንዲኖርም ለማድረግ ያግዛል›› ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የሚስተዋለው ችግር ለሁለቱም የሚበጅ አለመሆኑን የሚናገሩት ግደይ፣ ወጣቶቹ የፖለቲከኞቹን ግርግር ወደ ጎን በመተው የሁለቱን ክልል ሰላምና ወንድማማችነት ለማጠናከር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

‹‹ዝግጅቱን ለማሰናዳት በትግራይ ያለው የፖለቲካ ምህዳር ጠባብ ነው›› ያሉት ሙሉብርሃን ‹‹በአማራ ክልል ከሚገኙ ወጣቶች ተስፋ ሰጪ ምላሽ አግኘተናል›› ብለዋል።

ለመወያያነትም በተለይም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል በተፈጠሩት አሳዛኝና ተስፋ ሰጭ ክስተቶች ላይ የሚመክሩ ሲሆን፣ ከነዛ ታሪኮች ምን አግኝተናል፣ ምንስ ትምህርት ወስደናል፣ በቀጣይስ ምን ማድረግ አለብን በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያም እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል።

በትግራይ አማራጭ ሐሳቦች በማስተናገዱ፣ እንዲሁም ሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች በማክበሩ ረገድ ውስንነት እንዳለ ሙሉብርሃን ተናግረዋል፡፡ አክለውም ላለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ ጅማሮች መታየታቸው ተስፋን ቢፈጥርም በትግራይ እና አማራ ክልሎች መካከል የሚታየው ውጥረት ግን ያን ተስፋ የሚያደበዝዝ ነው ብለዋል።

ሁለቱን ክልልሎች በሚያዋስኑ ቦታዎች ላይ የሚከሰቱ ውጥረቶች አንድም የማንነት ጥያቄዎች ሌላም በማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ የበላይነትን የማግኘት ፉክክር ነው የሚሉ አስተያየቶች መኖራቸውን የሚናገሩት ዘርዐጽዮን የየክልሉ ፖለቲከኞች እና ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ አካላት ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ የሚሰነዝሩት አስተያየት ግን ችግሩን አባብሶታል ሲሉ ይደመድማሉ፡፡

ይህ አካሄድም ወዴት ያመራ ይሆን የሚል ስጋትን እንዳስከተለ አውስተው፣ ተጎራባች በሆኑት የአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካከል የሚታየውን ውጥረት እና ስጋት ለማርገብም የሚያስችሉ የተለያዩ ውይይቶችን ማካሄድ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

#አዲስማለዳ_ጋዜጣ

Report Page