#ETH

#ETH


የሰኔ 15ቱን የባህር ዳር ጥቃት ተጠርጣሪዎች ጉዳይ የሚመለከተው ፍርድ ቤት ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት ብርጋዴየር ጄነራል አሳምነው ጽጌን ወደ ጎንደር መስመር አጓጉዤያቸዋለሁ ያሉ ሹፌርን የምስክርነት ቃል አደመጠ። በጥይት ቆስለው ሆስፒታል የሚገኙት ሹፌሩ ፍርድ ቤት የቀረቡት በተሽከርካሪ ወንበር ነው።

የሹፌሩን የምክርነት ቃል ዛሬ ረፋዱን በነበረው ችሎት ያደመጠው በእነ ብርጋዴየር ጄነራል ተፈራ ማሞ መዝገብ የተጠረጠሩ 48 ሰዎችን ቅድመ ክስ እየተመለከተ የሚገኘው የባህር ዳር እና አካባቢው ፍርድ ቤት ነው። ፍርድ ቤቱ የአማራ ክልል አቃቤ ህግ አሉኝ ያላቸውን 17 ምስክሮችን ለማድመጥ ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም ዛሬ በችሎት የቀረቡት ሁለቱ ብቻ ናቸው። 

ሁለቱም ምስክሮች የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና ሌሎች ባለስልጣናት በባህር ዳር በተገደሉበት ዕለት መኪና የማሽከርከር የስራ ስምሪት እንደተሰጣቸው ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። በሰኔ 15 ብርጋዴየር ጄነራል አሳምነውን በመኪናቸው ማጓጓዛቸውን የተናገሩት አንደኛው ሹፌር ከዚያ አስቀድሞ ወታደሮችን ከቦታ ቦታ ሲያዘዋውሩ እንደነበር ተናግረዋል።

ብርጋዴየር ጀኔራል አሳምነውን ይዘው ወደ ጎንደር መስመር ሲጓዙ ባህር ዳር ዓባይ ድልድይን እንደተሻገሩ፣ እያሽከረከሩት ባለው መኪና ውስጥ እንዳሉ አንድ እግራቸውን በጥይት እንደተመቱ ገልጸዋል። እንደዚያ ቆስለውም ቢሆን ወደፊት መንዳት መቀጠላቸውን የተናገሩት ሹፌሩ በኋላ ግን ማሽከርከር እንዳቃታቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። በእሩምታ ተኩስ ሌላኛው እግራቸውን ሲመቱ ከመኪናው ወርደው መውደቃቸውን የተናገሩት ሹፌሩ በዚያን አፍታ ብርጋዴየር ጀኔራል አሳምነው ከመኪና ወጥተው መሄዳቸውን ለፍርድ ቤቱ አብራርተዋል።

ሌላኛው ምስክርም በእለቱ መኪና ተሰጥቷቸው ወታደሮችን ከቦታ ቦታ ሲያደርሱ እንደነበር እና መጨረሻ ላይ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ጽህፈት ቤት አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለችሎቱ ተናግረዋል። የመጀመሪያው ምስክር የባህር ዳር ጥቃት በተፈጸመበት ዕለት ስራ እንዲጀምሩ ቢደረግም ምንም ዓይነት ደመወዝ እስካሁን እንዳልተከፈላቸው ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሁለተኛው ምስክር ግን ለሹፍርና ስራቸው የሚከፈላቸው ደመወዝ አሁንም አለመቋረጡን ገልጸዋል። 

በዛሬው ችሎት የተጠርጣሪ ጠበቆች ባሰሙት ቅሬታ አቃቤ ህግ አሉኝ የሚላቸውን ምስክሮች በወቅቱ ማምጣት ባለመቻሉ የፍርድ ቤቱም ሆነ የጠበቆች ጊዜ በከንቱ እየባከነ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ትእዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ችሎቱ አቃቤ ህግ አሉኝ የሚላቸውን ምስክሮች በሚቀጥለው ችሎት አሟልቶ የማያቀርብ ከሆነ ከዚያ በኋላ ምስክር ለመስማት ጊዜ አይኖረውም ብሏል። ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የምስክሮችን ቃል ለማድመጥ ለነገ ነሐሴ 22 ቀጠሮ ሰጥቷል።

ችሎቱ ባለፈው አርብ በነበረው የፍርድ ቤት ቀጠሮ “የተጠርጣሪ ቤተሰቦች እንዲደበደቡ አድርገዋል” የተባሉ የፖሊስ ኃላፊን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለዛሬ እንዲያቀርባቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በችሎት ሳይገኙ ቀርተዋል። ይህንን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ኃላፊውን ባላቀረበው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ላይ “ምን እርምጃ ይወሰዳል የሚለው ወደፊት ይታያል” ብሏል። 

በእነ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ላይ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ቀን በይግባኝ የቀረበለት የባህር ዳር እና አካባቢው ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ለመወሰን ለከሰዓት በኋላ ቀጠሮ ሰጥቷል።

#dw

Report Page