#ETH

#ETH


በኤርትራ በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀስ የነበረው ”አፋር ኡጉጉሞ” የተባለው ድርጅት አመራሮች ትናንት በሰመራ ከተማ አቀባበል ተደረገላቸው።

የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ (አብዴፓ)ሊቀመንበር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳስታወቁት ድርጅቱ ከኤርትራ ወደ አገሩ የተመለሰው በመጋቢት 2011 በተደረገ ስምምነት ነው።

በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት የፖለቲካ ምህዳሩ በመጥበቡ ድርጅቶች ወደ ስደትና ትጥቅ ትግል መግባታቸውን አስታውሰው ፣ከነዚህም ውስጥ ከ41 ዓመታት በላይ ለአፋር ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች መከበር የታገለው ”አፋር ኡጉጉሞ” አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱ በሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ እንዲሁም አባላቱ በሂደት ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መሥራት ይገባዋል ብለዋል።

የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዓሊ መሐመድ ድርጅቱ የደርግ ሥርዓትን ለመጣል በተካሄደው የትጥቅ ትግል ተሳትፎ ለዴሞክራሲያዊት አገር ግንባታ ያደረገው ጥረት ውጤታማ ባለመሆኑ ወደ ትጥቅ ትግል መግባቱን ተናግረዋል።

የለውጡ ኃይል የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንዲሁም ፍትህን ለማረጋገጥ የወሰዳቸው እርምጃዎች በአገራቸው በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስታውቀዋል።

ድርጅቱ በሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ለክልሉ ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ለዴሞክራሲ መጎልበት ከክልሉ መንግሥት ጋር በመሥራት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አቶ ዓሊ አረጋግጠዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

#ena

Report Page