#ETH

#ETH


ለምህንድስና ተማሪዎችና በልምድ ለሚሠሩ ባለሙያዎች ስልጠና ሊሰጥ ነው!

ስልጠናው ከመስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ ይካሄዳል

ከዩኒቨርስቲ ለሚመረቁ የምህንድስና ተማሪዎችና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ዉስጥ በልምድ እየሠሩ ላሉ ባለሙያዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ሙያዊ ብቃት እንዲኖራቸዉ የሚያስችል ፕሮጀክት በጀርመን የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ማህበር መተግበር ጀመረ።

ፕሮጀክቱ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ጋር በትብብር ዳብሮ አሁን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት ላይ መሆኑን የጀርመን የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ሔንዝ ሪትማን ተናግረዋል።

በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ያሉትን ባለሙያዎች የዕዉቀት ክህሎት ለማሳደግ የሚረዳ ይሆናል ያሉት ሔንዝ የግንባታ ስራን ተግባራዊ ዕውቀት በኢትዮጵያ ዉስጥ ለማሳደግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸዉንም አያይዘው ገልጸዋል።

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ከዩኒቨርስቲ እና ከልዩ ልዩ ኮሌጆች የሚመረቁ ተማሪዋች የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ላይ ሰፊ ዕዉቀት ቢኖራቸውም ተግባራዊ እውቀት ላይ ግን አናሳ ናቸው›› ያሉት ሔንዝ፣ በሌላ መልኩ ደግሞ የኒቨርሲቲ ትምህርት ሳይኖራቸው በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን፣ በንድፈ-ሀሳቡም ሆነ በተግባራዊ ትምህርቱ ብዙ ገፍተውበት ባለመሄዳቸው ሁለቱንም ወገኖች በጋራ ተግባራዊ ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል›› ሲሉ ተናግረዋል።

ስልጠናው አንድ የኮንስትራክሽን ኩባንያ እንዴት ተመስርቶ ያድጋል፣ የቢዝነስ ፕላኑ እንዴት ይሠራል፣ የገንዘብ አቅሙን እንዴት ማሳደግ ይቻላል፣ ወደ ከፍተኛ ደረጃስ እንዴት ማሳደግ ይቻላል በሚሉና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

ይህ ስልጠና ከመስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከስልጠናው በኋላም አዳዲሶቹ ምሩቃን ተማሪዎች የየራሳቸውን የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በጋራም ሆነ በተናጠል በመክፈት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን አጋጣሚ እንደሚያመጣ ሚስተር ሔንዝ ይናገራሉ።

ለፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውለው ገንዘብ ከየጀርመን የገንዘብ ትብብርና ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የሚገኝ ሲሆን የሚያስተባብረው ሴኳ/Sequa/ የተባለው የጀርመን ድርጅት መሆኑንም ጠቁመዋል። ሃሳቡንም በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲም እንደደገፈ አያይዘው ገልጸዋል።

በዚህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊያን የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም አልፎ ለሀገርም በሙያው የዳበረ የኮንስትራክሽን ባለሙያ መፍጠር እንደሚያስችልና በሂደትም ከዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ጋር ተወዳዳሪ የሚሆኑ ድርጅቶችንም ኢትዮጵያ ውስጥ ማብቃት እንችላለን ብለዋል።

#ADDISMALEDA

Report Page