#ETH

#ETH


በሐዋሳ ከተማ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ሞተር ቢስክሌቶች ከዛሬ ጀምሮ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ተፈቀደ፡፡

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና የከተማዋ ፖሊስ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ኮማንደር ታደለ ዋሪዮ እንደገለጹት በከተማዋ ከአንድ ወር በፊት በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ላይ የታገደው እንቅስቃሴ ሕጋዊ ለሆኑት ተነስቷል።

እንደ ኮማንደር ታደለ ገለፃ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የከተማዋ ፀጥታ እየተሻሻለ በመምጣቱና አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ ኮማንድ ፖስቱ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ሞተር ቢስክሌቶች ብቻ በከተማዋ እንዲንቀሳቀሱ ወስኗል ፡፡

የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር መስፍን ዴቢሶ በበኩላቸው በከተማዋ መንቀሳቀስ የሚችሉት ሞተር ቢስክሌቶች የሰሌዳ ቁጥርና የሶስተኛ ወገን ያላቸው፣ ቦሎ የለጠፉ እንዲሁም አሽከርካሪዎቹ መንጃ ፈቃድ ያላቸው ብቻ ይሆናሉ ብለዋል ፡፡

ለፀጥታ ሥራ ልዩ ፈቃድ ከተሰጣቸው ሞተር ቢስክሌቶች ውጭ ሌሎች ሞተር ቢስክሌቶች ከንጋቱ 12፡00 እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት ብቻ መንቀሳቀስ እንደሚችሉም አስታውቀዋል ፡፡

በከተማዋ ከዚህ በፊትም ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ሞተር ቢስክሌቶች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ እንደነበር የገለፁት አዛዡ፣ ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመ በኋላ የተያዙትን ጨምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው ከነበሩት 628 ሞተር ቢስክሌቶች መካከል 444ቱ ባለቤቶቻቸው ሕጋዊ ሰነዶችን በማሟላታቸው እንደተመለሱላቸው ገልጸዋል ፡፡

ሕጋዊ ሰነዶች የሚያቀርቡ የሞተር ቢስክሌቶች ባለቤቶች ንብረታቸውን እንዲወስዱ ጠይቀዋል ፡፡

ሕጋዊ ሰነድ ሊቀርቡባቸው ያልቻሉ ሞተር ቢስክሌቶች ደግሞ በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል ውሳኔ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል ፡፡

በከተማዋ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴን ለመከላከልና ሰላምን ለማስጠበቅ የቁጥጥር ሥራ እንደሚሰራ የገለጹት ኮማንደር መስፍን፣ አሽከርካሪዎች የትራፊክ ፖሊሶች ሲያስቆሟቸውበመተባበርሕጋዊነታቸውን እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል ፡፡

የሐዋሳ ከተማ ፀጥታ ኃይልና በደቡብ ክልል የተቋቋመው ጊዜያዊ የፀጥታ ኮማንድ ፖስት ከሐምሌ 11 ቀን 2011 ጀምሮ በከተማዋ ላልተወሰነ ጊዜ ሞተር ቢስክሌቶች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱ ይታወሳል ፡፡

#ena

Report Page