#ETH

#ETH


በኢትዮጵያ የልብ ማዕከል ለልብ ቀዶ-ጥገና ህክምና ሰባት ሺህ ህፃናት ተራ እየጠበቁ መሆኑን ማዕከሉ አስታወቀ፡፡

በተለያዩ ሆስፒታሎች እና በየክፍለ-ሀገራቱ ያሉት ደግሞ ከዚህ በላይ ይሆናሉም ተብሏል።

የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር እና የልብ ሕሙማን ሕፃናት ስፔሽያሊስት የሆኑት ዶ/ር ሔለን በፈቃዱ፣ የሠለጠኑ ባለሙያዎች እና ዋና ዋና መሣሪያዎችም ማዕከሉ ውስጥ እያሉ በገንዘብ እጥረት ምክንያት አስፈላጊ የሆኑ አላቂ መድኃኒቶችን ማሟላት አለመቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ መሥራት ከሚችለው የቀዶ-ህክምና ሥራ ከአንድ ሦስተኛው በታች ብቻ እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን መሰል ቀዶ-ጥገና የሚሠራ ሌላ የግል ሆስፒታል ባለመኖሩም መክፈል የሚችሉት እንኳን ሕክምናውን ማግኘት አይችሉም፤ በተለይ ደግሞ መክፈል ለማይችሉ ብዙኃኑ ተስፋቸው በኢትዮጵያ የልብ ማዕከል ብቻ ነው።

ይህን ማዕከል ማጠናከር ማለት እነዚህን ታዳጊ ሕፃናት ነገ የሀገር ተረካቢ እንዲሆኑ ማስቻል እንደሆነ የዶ/ር ሔለን እና የብዙዎች እምነት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማዕከሉን በገንዘብ ለመደገፍ የአጭር የጽሑፍ መልክት /SMS/ ተጀምሯል።

በርካታ ኢትዮጵያውያንም በኢትዮ-ቴሌኮም ለዚሁ ዓላማ ብሎ በከፈተው 6710 ላይ መልእክቶችን በመላክ “አንድ ብር ለአንድ ልብ” በሚል የተጀመረውን በጎ ዓላማ በመደገፍ ላይ መሆናውን ዶ/ር ሄለን ገልፀዋል።

እንኢቢሲ ዘገባ ዶ/ር ሔለን በዚህ እንቅስቃሴ ላይ የየራሳቸውን ሚና የተጫወቱ ወገኖችን አመስግነው፣ ድጋፋቸው የአንድ ወቅት ዘመቻ ብቻ ሳይሆን ዘለቄታነት ያለው እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ እየተደረገ ያለው የመረዳዳት ጥሪም አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።

በአጭር የጽሑፍ መልእክት ከሚደረገው ድጋፍ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ በተጨማሪም ማዕከሉ በሦስት ባንኮች አካውንት በመክፈት እና በድረ-ገጹ ላይ የኦንላይን የገቢ ማሰባሰቢያ ገጽ /“Gofundme”/ በማዘጋጀት እየሠራ እንደሚገኝና መላ ኢትዮጵያዊያኑም በዚህ በጎ ተግባር እንዲረባረቡ ማዕከሉ ጥሪ አቅርቧል።

የባንክ አካውንቶቹም፦ CHFE (Children Heart Fund Ethiopia) በሚል የባለቤትነት ስም

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ቁጥር – 1000001839806

በአዋሽ ባንክ አካውንት ቁጥር – 01308236167000

በዳሽን ባንክ አካውንት ቁጥር – 0041600483011 ናቸው።

ድረ-ገጽ፦ www.chfe.org.et በመግባት የ/“Gofundme”/ ማስፈንጠሪያን (link)ን በመጫን እና ቀሪውን ሂደት በመከተል https://www.gofundme.com/3r5crk-50000… ድጋፍ ማድረግ ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ለመግባት የያዘውን እቅድ ለማሳካት ይረዳልም ተብሏል።

በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ አማካኝነት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ የዛሬ 10 ዓመት እውን የሆነው የልብ ማዕከል በኢትዮጵያ እስካሁን ለ4996 ሕፃናት ያለምንም ክፍያ የልብ ህክምና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

ይህም ህፃናቱ በትንሹ በውጭ አገራት ህክምናው ቢደረግ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ይጠይቅ እንደነበር ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

Via OBN

Report Page