#ETH

#ETH


የአሸንዳ በዓል ፍቅር፣ ይቅር ባይነትና መልካም ተግባቦት በተግባር የሚንጸባረቅበት በዓል መሆኑን ሁለት ጥናቶች አመለከቱ።

በትግራይ በተለያዩ አካባቢዎች ከነገ ጀምሮ በድምቀት የሚከበረውን የአሸንዳ በዓል ምክንያት በማድረግ በመቀሌ ከተማ የፓናል ውይይት ተካሂደ።

ዛሬ በተካሄደው የፓናል ውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሁለት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪዎች እንዳሉት፣ በዓሉ በልጃገረዶች ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት በድምቀት የሚከበር ነው።

የበዓሉ ይዘት በዋናነት በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ መልካም ተግባቦቶች፣ ፍቅርንና ይቅር ባይነት ላይ ያነጣጠረ መሆኑንም በጥናታቸው አመልክተዋል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህርና ተመራማሪ አቶ መብራህተን ገብረማሪያም ‘’የአሸንዳ በዓል ለሃገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት መረጋገጥ ያለውን ፋይዳ’’ የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በእዚህም በዓሉ ልጃገረዶች አደባባይ ወጥተው በጋራ የሚያከብሩት ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑን ነው የገለጹት።

በዓሉ የሌሎች ሃሳቦች፣ ጭፈራዎችና ትእይንቶችም እንዲታዩ የሚጋብዝ ከመሆኑ ባለፈ የሃይማኖትና የብሔር ልዩነት እንደማይንጸባረቅበት አመልክተዋል።

እንደ አቶ መብራህተን ገለጻ በአሸንዳ በዓል ላይ የሚነገሩ ስነ ቃሎች ይዘት በአብዛኛው ህብረትን የሚሰብኩ፣ መድልዎን የሚጠየፉና ለሰው ክብርን የሚያጎናጽፉ ናቸው።

“ልጃገረዶች በዓሉን በህብረሰቡ ውስጥ ያለውን እርስ በርስ የመተባበር፣ የመረዳዳትና የጀግንነት መልካም እሴቶችን አጉልተው ለማሳየት ይጠቀሙበታል” ብለዋል።

በተጨማሪም በህዝቡ ውስጥ ያሉትን ጉድለቶች በስነ ቃልና በዘፈን መልክ እንዲስተካከሉ የሚነቅፉበት፣ ማህበረሰቡ መድልዎን እንዲጠየፍ፣ የሴቶችን መብት የሚጋፋ የአስተዳደር መዋቅር አሊያም ወንድ ካለ እንዲስተካከል መልዕክት የሚያስተላልፉበት ጭምር መሆኑንም አመልክተዋል።

ፍቅርንና ትብብርን ከመስበክ ባለፈ በተግባር የሚያሳዩበት መድረክ መሆኑንም ተመራማሪው ጠቁመዋል።

“ይህም ለሀገር ግንባታ፣ አንድነት፣ ልማትና ሰላም መረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ ስላለው በአግባቡ መጠበቅና መጠቀም ይገባል” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዘርፉ ለቱሪዝም ልማት፣ ለባህል ግንባታ እና ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ እንዲውል ማድረግ እንደሚገባ አቶ መብራህተን አመልክተዋል።

‘’የአሽንዳ በዓልን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ስለሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎችና የሚስተዋሉ እጥረቶችን’’ በተመለከተ ጥናት ያቀረቡት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራመሪ የሆኑት ዶክተር አጽባሃ ገብረእግዛብሔር ናቸው።

በዓሉ ብዙ ሺህ ዓመታት ያስቆጠረና በርካታ ቱሩፋቶች ያሉት መሆኑን ጠቁመዋል።

‘’አሸንዳ ለትግራይ ህዝብ ባህል የመሰረት ድንጋይ ነው ‘’ያሉት ዶክተር አጽባሃ፣ በዓሉ ማንነትን አጉልተው የሚያሳዩ እሴቶች እንዳሉትም ገልጸዋል።

አሸንዳ ለሴቶች መብት አጥብቆ የሚታገል፣ መከባበርንና መረዳዳትን አብዝቶ የሚሰብክ፣ ሰዎች ባላቸው የሃብት መጠን ሳይሆን በሰውነታቸው ብቻ ክብር እደሚገባቸው በስነ ቃልና በዘፈን መልክ እንደሚያስተምርም ዶክተር አጽብሃ አስረድተዋል።

በተለያዩ የዓለም ሃገራት እንደ አሸንዳ ያሉት እና በሴቶች ዘንድ ብቻ የሚከበሩ ባህላዊ በዓላት መኖራቸውን ያመለከቱት ዶክተር አጽብሃ ፣ አንዳን አገራት በዓሉ በሰለጠነና ባህሉን በጠበቀ መልኩ ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ ፋይዳ በስፋት እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በዓሉ ሲከበር አልፎ አልፎ ጉድለቶች እንደሚስተዋሉ የጠቆሙት ተመራማሪው፣ በተለይ የባህል መበረዝ፣ በዓሉን አስመልክቶ ያልተገባ ተግባር መፈጸምና መሰል ችግሮች እንደሚፈጸሙና በወቅቱ ሊታረሙ እንደሚገባ አስግንዝበዋል።

ችግሮቹን ከመፍታት ባለፈ በዓሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራትና በዓሉን በተቋማዊ መንገድ መምራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

“በዓሉን ይበልጥ ማስተዋወቅ፣ የፋይናንስ አቅምን መገንባት፣ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ እንዲከበር ማድረግና ለበዓሉ በጎ ፈቃደኞችን ቁጥር ማብዛት ያስፈልጋል ሲሉም” ዶክተር አጽባሃ ገልጸዋል።

የአሸንዳ የልጅነት ጊዜያቸውን ለተሞክሮ ያስተላለፉት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ፈትየን አባይ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዓሉ ሴቶች ያላቸውን የፈጠራ፣ የመደራደር፣ የውሳኔ ሰጭነት ብቃት በተግባር የሚያሳዩበትና መልካም ስሜታቸውን የሚገልጹበት ነው ።

በአሁኑ ወቅት በዓሉን ምክንያት በማድረግ በአንዳንድ ልጃገረዶች ዘንድ ይፈጸማሉ የተባሉ ያልተገቡ ተግባሮችን በማረምና በማስተካከል በዓሉን ሳይበረዝና ሳይከለስ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም የድርኛውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

የፓናል ውይይቱን የከፈቱት የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርክቲ ገብረመድህን በበኩላቸው፣ በዓሉን በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ድርጅት በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ጥረቱ ከዳር እንዲደርስ የበዓሉ ዋና ባለቤት የሆኑትን ልጃገረዶች በዓሉን ሲያከብሩ በዓሉን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

#ENA

Report Page