#ETH

#ETH


በዳሽን ባንክ ጅማ ቅርንጫ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ያደረሱ ተከሳሾች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ተከሳሾች 1ኛአህመድ አብዶ፣ 2ኛ ጌቱ ወልደስላሴ፣ 3ኛ ዚያድ ሀሰን፣ 4ኛ የሱፍ ከድር፣ 5ኛ አንዋር ማሙድ፣ 6ኛ ገነት ሲሳይ፣ 7ኛ ሰይድ ሲራጅ፣ 8ኛ እንድሪስ ዓሊ እና 9ኛ ኦርጋኒክ ትሬዲንግ እና ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆኑ በፈፀሙት ከባድ የሙስና ወንጀልና በሙስና ወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

በዐቃቤ ሕግ ክስ እንደተመለከተው ሁሉም ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር 1ኛ ተከሳሽ በዳሽን ባንክ የጅማ መናኸሪያ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት ስራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሰራ የተሰጠውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ወንጀሉ እንዳይታወቅ የ5ኛ ተከሳሽን የይለፍ ቃል በመጠቀም እና የኮር ባንኪንግ ሲስተም ላይ ያለውን ስልክ በመለዋወጥ የባንኩን ገንዘብ በመመዝበር አስቀድሞ ወደ አዘጋጃቸው ግለሰቦች 2ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ሂሳብ ቁጥር አስተላልፎላቸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ገንዘቡ የተላለፈላቸው ተከሳሾች 18,100,000 ብር ወደራሳቸውና ወደሌሎች በሁለተኛ ክስ ዝርዝር ወደተገለፁት ሰዎች እንዲተላለፍ አድርገዋል፡፡

ተከሳሾች በተጠቀሰው መልኩ በአጠቃላይ 27,500,000 ብር ጉዳት በባንኩ ላይ ያደረሱ በመሆኑ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት ከባድ የሙና ወንጀል መከሰሳቸውን መዝገቡ ያሳያል፡፡

እንዲሁም 5ኛ ተከሳሽ የይለፍ ቃሉን ለ1ኛ ተከሳሽ በመስጠት የድርጅቱን ስራ በማያመች አኳኋን በመምራት የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡

በ3ኛ ክስ ከ6ኛ እስከ 9ኛ የተገለፁ ተከሳሾች በሙስና ወንጀል የተገኘውን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ ሲሉ ገንዘብ በመቀበል በይዞታቸው ስር በማድረግ፣ በመጠቀምና በመሰወር በቂ ካፒታል ያልተከፈለባቸውን ድርጅቶች በመመስረት የወንጀሉን ምንጭ ወደ ድርጅቶች ንብረት በማስተላለፍ፣ መልሶ ወደ ዋና ወንጀል አድራጊዎች በተለያዩ ባንኮች በማስገባት የገንዘቡን ትክክለኛነት፣ ምንጩን፣ ቦታውን፣ ዝውውሩንና የባለቤትነት መብቱን በመደበቅ ሂደት የረዱና ያመቻቹ በመሆናቸው በፈፀሙት የሙስና ወንጀል የተገኘን ገንዘብና ንብረት ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Report Page