#ETH

#ETH


ወታደሮችን አሳፍሮ ደቡብ ሶማሊያ ኪስማዮ ውስጥ ሊያርፍ ነበር የተባለ የኢትዮጵያ አውሮፕላን በኬንያ ኃይሎች በሚደገፉት የጁባላንድ ክልላዊ ወታደሮች መከልከሉን የዓይን ምስክሮች ገለጹ።

ወደ ኪስማዮ ያቀናው አውሮፕላን 'ከ90 በላይ ኮማንዶዎችን አሳፍሮ ነበር' የተባለ ሲሆን ተገቢውን መረጃ ቀድሞ አልሰጠም በሚል ምክንያት ነው እንዳያርፍ የተከለከለው ተብሏል።

ከምሥራቃዊ ኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ ተነስቶ ወደ ሶማሊያ እንደበረረ የሚነገርለት ይህ አውሮፕላን ኪስማዮ እንዳያርፍ በመከልከሉ ወደ ደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ በማቅናት ባይዶዋ ውስጥ እንዳረፈም ተነግሯል።

በኪስማዮ አየር ማረፊያ ሰራተኛ የሆነ ግለሰብ አውሮፕላኑ ከኢትዮጵያ መነሳቱንና በኋላም ወደ ባይዶዋ መሄዱን ለሮይተርስ አረጋግጧል። ነገር ግን አውሮፕላኑ የሲቪል ይሁን ወታደራዊ የታወቀ ነገር የለም።

"አውሮፕላኑ ወደኪስማዮ አየር ማረፊያ መጥቶ ለማረፍ ፈልጎ ነበር፤ ነገር ግን ቀድሞ መረጃ ስላልላከ የማረፍ ፈቃድ ተከልክሏል" ሲል የአየር ማረፊያው ሰራተኛ ለሮይተርስ ገልጿል።

በአካባቢው ሐሙስ ዕለት ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው ምርጫ ቀደም ብሎ በሶማሊያ ፌደራላዊ አስተዳደርና በክልሉ መሪዎች መካከል አለመግባባት እንዳለ ተነግሯል።

አውሮፕላኑ እንዳያርፍ መከልከሉ በኢትዮጵያና በኬንያ በሚደግፉት የፌደራልና ክልላዊው አስተዳደሮች መካከል ባለው ፍጥጫ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

ዳስላን የተባለ አንድ የግል ሬዲዮ ኪስማዮ ውስጥ የተከሰተውን ሁኔታ በተመለከተ ሲገልጽ በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለው ፉክክር ውጤት መገለጫ እንደሆነ አመልክቷል።

ከቀናት ኋላ በሚካሄደው ምርጫ በሥልጣናቸው ላይ ለመቆየት የሚወዳደሩት የጁባ ላንድ ፕሬዝዳንት አህመድ ሞሃመድ ማዶቤ የኬንያ ቁልፍ ወዳጅ ሲሆኑ ኢትዮጵያ ደግሞ መቀመጫውን ሞቃዲሾ ካደረገው የፌደራል መንግሥት ጋር ቅርበት አላት።

#BBCአማርኛ

Report Page