#ETH

#ETH


የተማሪዎችን ብቃት፣ ክህሎትና ተግባቦት በማጠናከር አጠቃላይ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ያስችላሉ ተብሎ የታመነባቸው አዳዲስ የትምህርት ዓይነቶች (ኮርሶች) በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ከመጪው ዓመት ጀምሮ የሚሰጥ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዚህም መሰረት ቀደም ሲል በሶሰት ዓመት ይጠናቀቅ የነበረው የመጀመሪያ ዲግሪ መደበኛ ትምህርት መርሃ ግብር ወደ አራት ዓመት ከፍ እንዲል ይደረጋል ተብሏል።

በትምህርት ጥራት ላይ በርካታ ችግሮች መኖራቸው በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጭምር የሚነሳና የቆየ ቅሬታ ነው።

ይህንኑ መሰረት በማድረግ መንግስት በዘርፉ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።

ከእነዚህም መካከል አንዱ አጠቃላይ የአገሪቱን የትምህርት አቅጣጫ የተመለከተው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ይጠቀሳል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ዙሪያ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን የሚተገበሩ የለውጥ ስራዎችን በተመለከተ እየተከናወኑ ያሉ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል።

ሚንስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በመግለጫው በአገር አቀፍ ደረጃ መግባባት የተደረሰባቸው በትምህርት ዘርፉ ላይ የተለዩ ችግሮችንና የፍኖተ ካርታ ጥናት ምክረ ሀሳቦችን መነሻ በማድረግ የሪፎርም ስራ በመከናወን ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ እንዳሉት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በልዩ ትኩረት እየተካሄዱ ካሉትና ከመጪው ዓመት ጀምሮ ወደተግባር ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት የለውጥ ሥራዎች መካከል አንዱ የከፍተኛ ትምህርት ስርዓተ ትምህርት ክላሳ ነው።

በፍኖተ ካርታው ዙሪያ በተካሄዱት ውይይቶችና ልዩ ልዩ የጥናት ውጤቶች መሰረት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ላይ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸው መረጋገጡን አመልክተዋል።

ከእነዚህም ክፍተቶች መካከል ተማሪዎቹ በተመረቁባቸው ሙያዎች የብቃትና ክህሎት ማነስ፣ የተግባቦትና የምክንያታዊነት ችግሮች፣ የቴክኖሎጂና የቀመር ክህሎት ውስንነት፣ የስራ ጠባቂነትና የጥገኝነት መንፈስ የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

የማህበረሰቡን እሴቶች ያለማክበር፣ ማህበራዊ ኃላፊነትን ያለመውሰድ፣ የስነ-ምግባርና የግብረ ገብነት ክፍተቶች መኖራቸውንም ፕሮፌሰር ሂሩት አክለዋል።

በመሆኑም በመጀመሪያ ዓመት የትምህርት መርሃ ግብር ላይ ልዩ የትምህርት ዓይነቶችን ለተማሪዎች ለመስጠትና የተጠቀሱትን ክፍተቶች ለማስተካከል ያስችላሉ የተባሉ የትምህርት ዓይነቶች ተለይተው መዘጋጀታቸውን ነው ፕሮፌሰር ሂሩት የገለጹት።

በዚሁ መሰረት በመጀመሪያ ዓመት መርሃ ግብር በሁሉም ዩንቨርስቲዎች ተመሳሳይ የትምህርት ዓይነቶች (ኮርሶች) እንደሚሰጡና ከሁለተኛ አመት ጀምሮም ተማሪዎቹ ወደተለያየ የትምህርት ክፍል እንደሚመደቡ ሚንስትሯ አብራርተዋል።

በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል በሶሰት ዓመት ይጠናቀቅ የነበረው የመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር ወደ አራት ዓመት ከፍ እንዲል የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል።

መርሃ ግብሩን በውጤታማነት ለመፈጸምም የመምህራን፣ የመጻህፍትና ሌሎች ግብዓቶችን የማዘጋጀት ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚደረገው ለውጥ በአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ጉዞ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበት መሆኑንም አክለዋል።

በመጪው የትምህርት ዘመን የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ብቻ ከ150 ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመጀመሪያ ዓመት ላይ የሚጀመሩት አዳዲስ የትምህርት ዓይነቶች ላይ የተደረገው የስርዓተ ትምህርት ለውጥ የሚመለከታቸውም እነዚህኑ አዲስ ተማሪዎች መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በመጪው የትምህርት ዘመን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ማረጋገጥ ይቻል ዘንድም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ፕሮፌሰር ሂሩት ተናግረዋል።

#ENA

Report Page