ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

የማንነት ፓለቲካና የኢትዮጵያ ሚዲያ

" የማንነት ፓለቲካና የኢትዮጵያ ሚዲያ" በሚል ርዕስ የሚዲያ ባለሞያዎችንና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ዛሬ ተዘጋጅቶ ነበር። በውይይቱም መነሻ የሚሆን ጹሑፍ ቀርቦ የነበረ ሲሆን ተሳታፊዎችም በተነሱ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ሚዲያዎች በማንነት ላይ ተመስርተው መቋቋማቸው በራሱ ችግር እንዳልሆነ የገለጹት ተሳታፊዎቹ መስፈርቱ የሞያ ሥነ-ምግባሩን ጠብቆ መጓዝ ሊሆን እንደሚገባ ነው ሃሳባቸውን የሰጡት።

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩትና አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) ሚዲያዎች በምን አይነት መልኩ ተደራጁ የሚለው ሳይሆን በአንድ አከባቢ ያሉ ሰዎችን እኩል ያገለግላሉ ወይ? የሚለው ላይ ነው ማተኮር የሚያሻው ሲሉ ገልጸዋል። ሚዲያዎች አንድን ማንነት ወክለው እንዲደራጁ ህጉ እንደማይከለክል ጭምር ጠቅሰዋል።

ተመሳሳይ ሀሳቡን ያንጸባረቀው የኦሮሚያ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ናዚፍ ጀማል "አሁንም ቢሆን በቋንቋቸው ሚዲያ ያልተከፈተላቸው አሉ" ሲል ብሔርን መሰረት ያደረገ ሚዲያ መቋቋሙ ብቻውን ችግር እንዳልሆነ ያነሳል። እንደ ናዚፍ አስተያየት የአንድን ወገን ሃሳብ ብቻ ማቅረብ፣ የጋዜጠኞች ስሜታዊ ተሳትፎ (emotional involvement ) እና ቅድመ ትንበያ የተቀመጠላቸውን ጥያቄዎች/እንግዶች ማቅረብ በአጠቃላይ ባሉት ሚዲያዎቻችን የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው ሲል ያስቀምጣል።

ውይይቱ " የማንነት ፓለቲካና የኢትዮጵያ ሚዲያ " በሚለው የውይይት ርዕስ ላይ መሰረት ቢያደርግም በአጠቃላይ በሀገራችን ባሉ ሚዲያዎች የሚስተዋሉ ችግሮችና ማነቆዎች ጭምር ከተሳታፊዎች ተነስተዋል።

በዋናነት ከተነሱት ጭብጦች መካከልም አንዱ የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባርን አለማክበር ሲሆን እንደ ፋሲካ ታደሰ ገለጻ ማህበራት ይህንን ከማስከበር አንጻር ከፍቸኛ ድርሻ እንዳላቸው ትጠቅሳለች። ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ ወርቃየው ቸኮል በበኩሉ አሁን ላይ ሚዲያው የፓለቲካው ኢኮኖሚ ነጸብራቅ በመሆኑ ሞያዊ ሥነምግባሩን ተከትሎ ለመስራት አዳጋች እንደሚያደርገው ነው ያነሳው።

ከዚህ በተጨማሪም የሚዲዎች የገንዘብ ምንጭና ፈቃድ አሰጣጥ ሂደት ትኩረት እንዲሰጣቸው ከተሳታፊዎች ከተጠቆሙ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።

አሁን ላይ በመንግሥት ሚዲያዎችም ሆነ በሌሎች ሚዲያዎች የሚታየው ወገንተኝነት በራሱ ትልቅ ችግር መሆኑንና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለመቀነሱ፤ ሚዲያው ራሱን የሚገመግምበት ሥርዓት አለመበጀቱ፤ የሥልጠናዎች ማነስና ተግባራዊነታቸው ላይ ክፍተት መኖሩ፤ የሥርዓተ ትምህርቱ ድክመት፤ የህግ ማዕቀፎች ክፍተት፤ የመረጃ ነጻነት ገደብና የሚዲያ አስተዳደር ድክመት ሌሎችም እንደክፍተት የተለዩ ጉዳዮች ናቸው።

በአንጻሩ ደግሞ ሚዲያው ራሱን የሚገመግምበት አውድ መፍጠርና የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት መቀነስ፤ ሞያዊ በቃትን ማሳደግ፤ ማህበራትን ማጠናከር፤ የትምህርት ሥርዓቱን ማሻሻል፤ የሚዲያ አስተዳደርና ኦዲቶሪያል ፓሊሲን ማጠንከር፤ የሚዲያ ግንዛቤን ማስፋትና የሚዲያዎችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጠናከር ለተጠቀሱት ክፍተቶች በመፍትሔነት ከተወያዮቹ የቀረቡ ኃሳቦች ናቸው።

መድረኩን መርሳ ሚዲያ ኢንሲቲቲውት፤ የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር፤ የኢትዮጵያ የማህበረሰብ ራዲዮ ጣቢያዎች ማህበር እና ኢናሚሳ በትብብር አዘጋጅተውታል።

#𝕥𝕚𝕜𝕧𝕒𝕙-𝕞𝕒𝕘𝕒𝕫𝕚𝕟𝕖

Report Page