ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

የወላይታ ዞን ምክር ቤት 4ተኛ ዙር 7ተኛ ዓመት 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በጠራው ስብሰባ ያወጣው የአቋም መግለጫ

የወላይታ ሕዝብ የኢፌዴሪ ሕገመንግስት መሠረት አድርጎ ራስን በራስ የማስተዳደርና ክልል የመመስረት መብት ተግባራዊ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበረ ይታወቃል። ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ወላይታ ብሔር ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት እንደሚገባው ህገ መንግስቱ በግልጽ ብደነግግም የክልሉ ምክር ቤት የወላይታን ክልል የመመስረት ጥያቄን ለምክር ቤት እንደ አጀንዳ ላለማቅረብ በማሰብ መደበኛ ስብሰባዎችን በተደጋጋሚ ሆን ብሎ እየዘለለ ቆይቷል፡፡   

ከዚህም ባሻገር የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ የምክር ቤት ጉባዔ ጊዜ ካሳለፈ በኃላ ባካሄዳቸዉ አስቸኳይ ጉባዔዎች የወላይታ ህዝብ ጥያቄ ለጉባዔው እንዳይቀርብ የተደረገ ሲሆን የወላይታ ህዝብ ተወካዮች በምክር ቤቱ አጀንዳ ለማስያዝ ከፍተኛ ጥረት ብያደርጉም ታፍነዉ ዕድል እንዳይሰጣቸዉ ተደርገዋል፡፡

ይህንን ኢፍትሐዊ አሠራር መነሻ በማድረግ የወላይታ ዞን ምክርቤት በዛሬው ዕለት አስቸኳይ  ጉባኤ የጠራ ሲሆን በዚህ አስቸኳይ ጉባዔ በዋናነት የዞኑ መስተደድር የሕዝቡን ክልል የመመስረት ጥያቄን የመራበት ሂደት በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን እስካሁን ያለው ሂደት አመርቂ መሆኑንም ገምግሟል፡፡ 

በዚህም መሠረት ምክርቤቱ  በስፋትና በጥልቀት ከተወያየ በኃላ የሚከተለዉን ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አዉጥቷል፤

1.  የወላይታ ሕዝብ በኢፌደሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 47 (3) መሠረት የጠየቀዉ የራሱን ክልል የመመስረት መብት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሆን የሚመሰረተዉ ክልል ስያሜው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የሥራ ቋንቋ ወላይትኛ (Wolaittatto Doona)፣ የክልሉ ርዕሰ-ከተማ ‹‹ወላይታ ሶዶ›› ይሆናል፡፡ ስለሆነም መንግስት ሕገ-መንግስታዊ ለሆነ ህዝብ ጥያቄ ህገ-መንግስትን በተከተለ መንገድ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ የወላይታ ብሔር ምክር ቤት አጥብቆ ይጠይቃል፡፡

በተጨማሪም ይሄ ጥያቄ በጊዜ ባለመመለሱ የተነሳ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰ፣የዞኑ መንግስት ሙሉ ጊዜውን በልማት ሥራ እንዳያውል እንቅፋት እየሆነ የሚገኝ በመሆኑ ሂደቱም ወደ ፀጥታ ችግር ሳይሸጋገር የፈደራል መንግስት ኃላፊነት ወስዶ ምላሽ እንዲሰጥ ምክርቤቱ ጠይቋል።

2.  የወላይታ ብሔርን ወክለዉ በክልል ምክር ቤት ሲሳተፉ የነበሩ የወላይታ ህዝብ ተወካዮች በቀን 11/10/2012 ዓ.ም የክልሉ ምክር ቤት ባካሄደዉ 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባዔ ላይ ላለመሳተፍ ራሳቸዉን ከምክር ቤት አባልነት ማግለላቸዉ ለሁሉም ኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ ነዉ፡፡ ይህንን ያደረጉበት ምክንያት የክልሉ ምክር ቤት ለወላይታ ህዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ባለመስጠቱ ነዉ፡፡ ይህ የወላይታ ብሔር ተወካዮች ዉሣኔ ለወላይታ ብሔር ያላቸዉን ክብር የሚያሳይ ስለሆነ ምክርቤቱ በአድናቆት ተመልክቷል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ተወካዮች የክልሉ አስተዳደርና የክልሉ ምክር ቤት ጠርተዉ ማወያየት ሲገባዉ እስካሁን ድረስ ዝም ማለቱ መላዉን የወላይታ ሕዝብ አለማክበሩን ያሳያል፡፡  የሕዝብ ውክልና የያዘ አካል ለክልሉ ምክር ቤት ያለዉን ቅሬታ ለማሳየት መልቀቂያ ቢያስገባ የዚህን ሕዝብ ተወካዮች ጠርቶ አለማወያየትና ተገቢ ትኩረት አለመስጠት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ የወላይታ ሕዝብ በሀገሪቱ ለመጣዉ ለዉጥ ትልቅ ዋጋ የከፈለ ታሪክ ያለዉ ሕዝብ ነዉ፡፡  ስለዚህም የፌዴራል መንግስት እነዚህን የወላይታ ህዝብ ተወካዮችን ጠርተዉ እንዲያነጋግር የዞኑ ምክር ቤት አጥብቆ ይጠይቃል፡፡

3. የደቡብ ክልል ምክርቤት የሚወስናቸው ወላይታን የሚመለከት ማነኛውም ውሳኔ ተግባራዊ ከመሆናቸው አስቀድሞ በዎላይታ ዞን ምክርቤት ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት ወስኗል። በተጨማሪም በክልሉ መስተዳድር ምክርቤት የሚወስኑ የወላይታ ህዝብ ጥቅም የሚጎዱ ማነኛውም ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን ምክርቤቱ ወስኗል።

4.  የደቡብ ክልል ፀጥታ መዋቅር የሚመሩ አካላት ላይ እምነት ስለለንና ገለልተኛ ባለመሆናቸው እንዲሁም የክልሉ ፀጥታ ሥራ በኮማንድ ፓስት የሚመራ በመሆኑ የወላይታ ዞን ፀጥታ ሥራ በህዝቡ እና በዞኑ ፀጥታ መዋቅር ጋር በትብብር መፈፀም እንዳለበት እና ድጋፍ በሚያስፈልግበት ጊዜ ከፈደራል ፀጥታ መዋቅር በትብብር መሠራት እንዳለበትም ተወስኗል።

5. ወደፊት የሚመሰረተው የወላይታ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊ እና ፓለትካዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ህጎችን ፣ደንቦችን፣አዋጆችንና መመሪያዎችን እንዲያዘጋጅ ሰክራቴሪያት ፅ/ቤት እንዲቋቋም ተወስኗል። በተጨማሪም የዞኑ መንግስት እንደየአስፈላጊነቱ ለወላይታ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምስረታ የሚያግዙ ተቋማትንና ግብረሀይሎችን በማቋቋም ሂደቱን በበላይነት እንድመራም ተወስኗል። 

6 . ቀጣይ ህዝባዊ ጥያቄ ሰላማዊ፣ህጋዊና ድሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ ተወስኗል።

 7. የወላይታና አጎራባች ህዝቦች ትስስር ለዘመናት የቆየና በቀጣይ አብሮ የሚኖርና የህዝቦች ትስስር ከመዋቅር በላይ በመሆኑ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የዞኑ ምክርቤት ወስኗል።

ለመላዉ የወላይታ ህዝብ የራሱን ክልል የመመስረት ህገ-መንግስታዊ መብት በሚመለከተው ፌዴራል መንግስት አካል ለጥያቄዉ ተገቢ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ እንደተለመደው ሁሉ ሠላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የወላይታ ዞን ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል፡፡

"የኢፌዴሪ ህገ-መንግስትና ዓለማቀፍ ህግ ያጎናጸፈዉ የወላይታ ህዝብ ክልል የመመስረት መብት ጥያቄ በሰላማዊ ህዝብ ትግል እውን ይሆናል!"

ሰላም ለሀገራችን 

የወላይታ ዞን ምክርቤት 

ወላይታ ሶዶ፣ ኢትዮጵያ 

  15/10/12 ዓ ም

Report Page