ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው ድርድር ቀጥሏል

የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሚዲያዎች በላከው መግለጫ ኢትዮጵያ በድርድሩ ሁለት የቴክኒክና የህግ ቡድኖች ቢኖሩ በሚል ያቀረበችውን ሀሳብ ሱዳን መቀበሏን አመልክቷል።

በግብፅ በኩል ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ሳትቀበለው የቀረችውን ረዘም ያለ የድርቅ ጊዜን እና ደረቃማ ዓመትን በተመለከተ ዝርዝር ህግ መኖር አለበት የሚለውን ሃሳቧን በድጋሚ አንስታለች።

በእለቱ በነበሩ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በተካሄደ ድርድር ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ ባቀረበችው ሃስብ ላይ ንግግር መደረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በዚህም መሰረት የመጀመሪያው ዙር የግድቡን የውሃ አሞላል እና አሞላሉ የሚገዛበት መመሪያን በተመለከተ ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሃሳብ ለመቀጠል ከመግባባት መደረሱን ነው ያመለከተው።

ረዥም ድርቅን በተመለከተ የቴክኒክ ኮሚቴ የውሃ አለቃቁ ላይ ህግን እንዲያዘጋጅ ሃላፊነት እንዲሰጠው እና ዝርዝር አለቃቀቅን በተመለከተ ግን ድርድር እንደሚያስፈልግ ከመግባባት ላይ ተደርሷል።

እንደዚሁም የግድቡን ደህንነት የተመለከተ ህግ እና ግድቡ በሚኖረው አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ተፅእኖ ጥናት ማስፈለግ ላይ ተግባብተናልም ነው ያለው መግለጫው።

የግብፅ ተደራዳሪዎች በእለቱ የነበራቸው ተሳትፎ የተቀዛቀዘ ነበር ያለው መግለጫው፥ ከተራዘመ የድርቅ ሁኔታ ጋር ያላቸውን ፍላጎት በማሳወቁ ላይ ብቻ መሳተፋቸውን አመልክቷል።

ሆኖም በመጨረሻ ሰዓት የግብፅ ተደራዳሪዎች ውይይት ሲደረግበት በነበረው እና ከዚህ በፊት ራሳቸው ሊያሰራ የሚችል ሰነድ ነው ብለው አስተያየት የሰጡበትን ሱዳን ያቀረበችውን ሰነድ መልሰው ተቃውመዋል።

በተጨማሪም የራሳቸውን አቋም ይዘው እንዲቀርቡ መጠየቃቸውን የተቃወሙት ግብፃውያኑ፥ ድርድሩ እየተካሄደ የግድቡ ውሃ ሙሌት ሊካሄድ አይገባም ሲሉ ተቃውመዋል።

እንደዚሁም እየተካደ ያለው ድርድር ሰኞ እንዲጠናቀቅ እና እስካሁን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያስቀመጧቸውን ብድርድሩ ለተገኙ ለውጦች እውቅና ላለመስጠት ፍላጎት ታይቶባቸዋል ነው ያለው።

ድርድሩ ዛሬም እንደሚቀጥል የጠቆመው ሚኒስቴሩ የተደረጉ ድርድሮችን መሰረት በማድረግ በተዘጋጁ መመሪያዎች እና ህጎች ላይ ሀሳብ ይለዋወጣሉ ብሏል።

Report Page