ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

አይዴ ጫምባላላ / Ayidde Chamabalalla!!

(የመልካም ምኞት መግለጫ)

ከሁሉ በማስቀደም ለሲዳማ ህዝብና ለመላ ኢትዮጵያውያን  እንኳን ለሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ እያልሁ በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆንላችሁ በራሴና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ባህልናቱሪዝም ሚኒስቴር ስም ከልብ እመኛለሁ፡፡ 

አይዴ ጫምባላላ / Ayidde Chamabalalla!!

የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ፍቼ ጨምበላላ ከጥንት ጀምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ ከነሙሉ ክብሩ ዛሬ ላይ የደረሰ ደማቅና የኩራታችን ምንጭ የሆነ ባህላዊ ዕሴታችን ነው፡፡ ዛሬ ላይ በዓሉ የሲዳማ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን ከዚያም አልፎ የዓለም ህዝቦች ሁሉ ሃብት ሆኖ ይገኛል፡፡ ለቀደምት አባትና እናቶቻችን ክብር ይግባቸውና ይህንን የመሰለና ለአገራችን እንደ ውብ ፈርጥ አምረውና ጎልተው ከሚታዩ በዓላት አንዱ የሆነውን ይህንን ባህላዊ ዕሴት ለዚህ ትውልድ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡

ይህ በዓል ከዘመን መለወጫ በዓልነቱ ባሻገር የሲዳማ ህዝብ ጥልቅ የሆነ ማህበራዊና ምጣኔሃታዊ እሴቶች መገለጫም ጭምር ነው። ባህላዊ ሁነቱ በዋናነት  ሰላምን፣ መከባበርን፣ አብሮ መኖርን፣ መቻቻልን፣ ልማትን፣ እርቅን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያከብር ትልቅ ሀብት ነው፡፡ 

ፊቼ ጫምባላላ ስለ ሠላም የሚሠጠው ከፍ ያለ ቦታም በሠው ልጆች ላይ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ስጦታዎችም ጭምር የሠላም አየር እንዲነፍስ የሚያደርጉ እሴቶች በውስጡ አጭቆ የያዘ ነው።  ፊቼ ጫምባላላ  አብሮ በመኖር ሂደት መጋጨት እንደ ምድር የስበት ሕግ የማይቀር መሆኑን በጥልቀት በመረዳት የግጭት አፈታት "አፊኒ"  በተሰኘ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሥርዓት ግጭቶችን በማስወገድ እርቅና ሰላም እንዲወርድ በማድረግ የሚከበር በዓል ነው።

ህፃናትና ሴቶች ዓለም አሁን ከተኛበት ተነስቶ የእኩልነት መብትና የፆታ ጉዳይ እያለ ከመስበኩ አስቀድሞ ሲዳማ በፊቼ ጫምባላላ አክብሮቱን ሲያሳይ ብዙ አመታትን ያስቆጠረ ነው። በፊቼ በ"ሁሉቃ" የመሽሎክ ምሥጢር በድርጊትም በምሳሌም የተገለጠ የሽግግር እና የዘመን መለወጥ ታላቅ ማሳያ ነው። ፈጣሪ በአምሳሉ  ለፈጠረው ሠው ብቻ ሳይሆን ፊቼ ጫምባላላ እንስሳቶችንም እንደሚያከብር ተረድተናል።

በዚህ ቀን እንስሳቱ እንኳን ቢላዋ ሊያርፍባቸው ይቅርና አርጩሜ እንኳን አይነካቸውም ይልቁኑም እንደ እንግዳ እነሱም የተለዬ ገበታ ተሠናድቶላቸው በለምለም ሣር ላይ ጨዋማ አፈር ወይም "ቦለ" እንዲጋበዙ እንደሚደረግ ዐይተናል፡፡ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ የአንድነትና የፍቅር ተምሳሌት በመሆን ከህፃን አስከ ሽማግሌ በፍፁም ደስታ የሚከበረው ይህ ታላቅ በዓል ከነሙሉ ክብሩና ለዛው ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ መሸጋገር ይኖርበታል፡፡ አሁን ያለው ትውልድ አደራም ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት መቻል ነው፡፡

ለዚህም ባህላዊ ዕሴቱ በውስጡ አቅፎ የያዛቸውን ከላይ የተጠቀሱትንና መሰል ጠቃሚ ትሩፋቶችን ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ በጽሁፍ፣ በምስል እንዲሁም በምስልና ድምፅ ከትቦ መያዝና ከትውልድ ትውልድ ለማሸጋገር በሚያስችል መልኩ ሰንዶ ማስቀመጥ የዘርፉ ምሁራንና የአካባቢው ማህበረሰብ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

ይህንን ማድረግ ከተቻለ የሲዳማ ሕዝብ  ለዘመናት አብሮ በመኖርና በሥራ ያዳበራቸውን ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ ክንዋኔዎችንና አስተሳሰቦችን ጠብቆ ማቆየት ይቻላል። ከዚህ ባሻገር ሁነቱ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ከማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ዓለም በቅርሶች መካከል አንዱ እንዲሆን በማድረግ የመዘገበው በመሆኑ በዓለም ህዝቦች ዘንድ እየታወቀ ይገኛል፡፡

ይህን መልካም ዕድል በዓሉን ይበልጥ በማጎልበትና ሳቢ በማድረግ ጎብኝዎች ወደ አካባቢው ብሎም ወደ አገራችን እንዲመጡ በሂደቱም ባህላዊ ሁነቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ማህበራዊና ምጣኔሃብታዊ ጠቀሜታ እንዲያስገኝ ለማድረግ አቅዶ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላትና የአካባቢው ማህበረሰብ እጅ ለእጅ ተያይዘው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

ሁላችሁም እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም ፊቼ ጫምባላላ በተለያዩ ሥነሥርዓቶች ታጅቦ ያለማቋረጥ ለረጅም ዘመናት በድምቀት ሲከበር የቆየ ውብ ባህላችን ነው። የዘንድሮ ፊቼም ከግንቦት 12-13/2012 ዓ.ም የሚውል ቢሆንም ያለንበት ወቅት አስከፊው የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ብሎም በሀገራችን በተከሰተበት  ወቅት ላይ የምንገኝ በመሆኑ ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው በ"ጉዱማሌ" ወይም በባህላዊ አደባባይ፣ በቄጣላና በተለያዩ ውብ ባህላዊ ክንዋኔዎች የሚከበር አይሆንም።

ይህንን መነሻ በማድረግም ሁሉም የብሔሩ ተወላጆች በዓሉን በየቤታቸው እንዲያከብሩ የሲዳማ አባቶች ባህሉ በሚፈቅደው መሠረት ውሳኔ እንዳስተላለፉ ተረድተናል። ይህም የአባቶቻችንን ብልህነት፣ አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት በግልፅ ያሳየ በመሆኑ በዚሁ አጋጣሚ ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

በአጠቃላይ ያለንበት ወቅት ከመቸውም ጊዜ በላይ መተባበርንና መደጋገፍን የሚጠይቅ መሆኑን ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡ ፍቼ ጨምበላላ የፍቅርና የመተሳሰብ ተምሳሌት እንደመሆኑ በዚህ ወቅት ኮቪድ 19 ባስከተለው ጫኛ የተነሳ ኑሯቸው የተናጋባቸውን ወገኖች በያሉበት አለሁላችሁ በማለትና የሚፈልጉትን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ከጎናቸው ልንቆምና ልንታደጋቸው ይገባል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን መንግስት የህዳሴውን ግድባችንን ጨምሮ ሌሎች ልማታዊ እቅስቃሴዎች እንዳይስተጓጎሉ ለሚያደርገው ጥረት የየበኩላችሁን ድርሻ በማበርከት የአገራችንን ከፍታ ዕውን ለማድረግ እንድትተጉ  በታላቅ አክብሮትና ትህትና አደራ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ ጫምበላላ ከአንዱ ዘመን ወደሌላው መሻገርን የምናበስርበት እንደሆነ ሁሉ በዚህ ፈታኝ ወቅት ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ልብ ለልብ ተሳስረን አገራችንን ከዚህ ፈታኝ ዘመን ለማሻገር ቆርጠን እንነሳ ለዚህም ፈጣሪችን ይርዳን እላለሁ፡፡     

በያለንበት በዓሉን ስናከብር ራሳችንን ከኮሮና ወረርሽኝ እየጠበቅን ይሁን፡፡

በድጋሚ በዓሉ ለሁላችሁም የሰላም የጤናና የስኬት እንዲሆንላችሁ እንመኛለሁ።                             

ፊቼ ጄጂ ጄጂ!

ሒሩት ካሳው ወንድም (ዶ/ር)

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር

Report Page