ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የበላይ ጠባቂ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ

በየዓመቱ  ሚያዝያ  30  የዓለም  ዓቀፉ  ቀይ  መስቀልና  ቀይ  ጨረቃ  ቀን ይታሰባል፡፡ በዓሉ  ለመጀመሪያ ጊዜ ታስቦ መዋል ከጀመረበት እ.አ.አ ከ1948 አንስቶ የሰዎችን ክብር ፤ጤናና  ደህንነት  መጠበቅ  እንዲሁም  ለተቸገሩ  የመድረስ  እሳቤዎችን በጉልህ ሲያንጸባርቅ  እና ሲተገብር ቆይቷል፡፡ ይህ ዓለም ዓቀፋዊ የጋራ መግባባት የተያዘበት ሰብዐዊ እንቅስቃሴ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ከችግር እና ከስቃይ የገላገለ፤በሽታዎችን የፈወሰ፤ለተንገላቱት የተረጋጋ ሕይወት የሰጠ ድንቅ ተግባር ነው፡፡ በዓለማችን ላይ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ደግሞ ይህን የሠብዓዊነት መንፈስ እጅግ በተጠናከረ መንገድ እንድናድሠው ግድ የሚልበት ሁኔታ ላይ አድርሶናል፡፡ 

የዘንድሮው የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀን "ለጤና ባለሙያዎቻችን እጅ እንነሳለን፤ እናደንቃችኋለን" የሚለው መሪ ቃል እጅግ አግባብ የሆነ፤ ትክክለኛ መልዕክት ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ትተው፤ ሕይወታቸውን አደጋ ውስጥ ከተው ፤ከወረርሽኙ ጋር የመጀመሪያ ተፋላሚ የሆኑት የህክምና ባለሙያዎቻችን የሚከፍሉት መስዋዕትነት ሌላው ድንቅ አርበኝነት ነው፡፡

በ1927 ዓ.ም የተመሰረተው አንጋፋው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ኮቪድ-19 የሚያስከትለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ለመከላከል የሚደረገውን ሀገራዊ ርብርብ በተጨባጭ  በመደገፍ  ላይ ይገኛል፡፡ በተለያዩ ከተሞች ቫይረሱን ለማጽዳት  የኬሚካል ርጭት በማከናወን፤ለህብረተሰቡ ድጋፍ የሚሰጡ በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት፤ የንፅህና መጠበቂያዎችን በማሰራጨት እና የማኅበሩ አምቡላንሶችን ለህብረተሰቡ አገልግሎት ዝግጁ በማድረግ ያሳየው ተነሳሽነት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ 

ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በጤና ሚኒስቴር ይፋ የተደረጉት ቁጥሮች ቀጣዮቹ ቀናትና ሳምንታት ምን ያህል እየከበዱ ሊመጡ እንደሚችሉ በግልጽ አመላካች ናቸው፡፡አሁንም ማህበረሰቡ በመንግስትና በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክሮች በጥብቅ እንዲተገብር፤ ብሎም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶች በምንፈልገው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆኑ ቀንና ሌሊት መስራት የግድ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርም  በመላ ሀገሪቱ የዘረጋቸውን መዋቅሮች በመጠቀም ማህበረሰባዊ  ተሳትፎ እንዲጎለብት ፤ በይበልጥም ደግሞ የበጎ ፈቃደኝነት እና የመልካም ዜጋ ባህል እንዲሰፋ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ታች ቀበሌ ድረስ የሚገኘውን መዋቅሩን በመጠቀም ህብረተሰቡን ሊያነቃ ፤ሊያስተምር እንዲሁም  የሚታይ፤ የሚጨበጥ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ  የጀመራቸውን ሥራዎች ማጠናከር ይኖርበታል፡፡ በዚህ አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎችን አለሁላችሁ ማለቱን መግፋት አለበት፡፡ ይደመጣልና!

የገጠመንን ጠላት ለመከላከል ማህበረሰባዊ ንቃትና ተሳትፎን ማጠናከር ቁልፍ ተግባር ነው፡፡ ኮቪድ-19 አንዳችን ለሌላችን በእጅጉ የምናስፈልግበትን ምክንያት እንዲሁም ፈተናዎቻችንን በተናጠል ሳይሆን በቅንጅት ድል መንሳት እንደምንችል ቁልጭ አድርጎ ያሣየን ታሪካዊ አጋጣሚ ሆኗል፡፡ ተባብረንና ተሠባስበን የጋራ ክንዳችንን በማሳረፍ ራሳችንንም ሆነ ሀገራችንን ከወረርሽኙ እንታደግ፡፡ 

ሚያዝያ 30/2012 ዓ.ም

Report Page