ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

                  

ለመላው የኢትዮጵያ ሠራተኞች የመልካም ምኞት መግለጫ  

ከሁሉ አስቀድሜ በአገራችን ለ45ኛ ጊዜና በዓለማችን ለ131ኛ ጊዜ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ሜይዴይ ክብረ በዓል እንኳን በሠላም አደረሳችሁ እያልኩ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቴን በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና በራሴ ስም ላስተላልፍላችሁ እወዳለሁ፡፡

የዓለም ሠራተኞች ቀን የትግል ደወልና የድል አርማ የሆነው ሜይዴይ ምዕተ ዓመታትን እያጣቀሰ በዘለቀ እድሜው ትውልድ ተቀባብሎታል፡፡ ሜይዴይ የኣለም ላብአደሮች ያለፉበትን የትግል ውጣውረድና የጨበጡትን ድል የሚያስቡበትና መጪውን ብሩህ ዘመን አሻግረው የሚያስተውሉበት ቀን በመሆኑ የሥራው ዓለም ተዋንያንና የልማት አጋሮች በጋራ ስናከብረው ደስታ ይሰማናል፡፡

ሠራተኛው ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ ተጠብቆ የላቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን እየታገለ የከፈለው መስዋትነት ሜይዴይ በተከበረ ቁጥር ሲዘከር ይኖራል፡፡ ጨቋኝና በዝባዥ ስርዓትን ከለላና መከታ ያደረጉ አሠሪዎች በሠራተኛ ላይ የሚፈፅሙትን ግፍና በደል ለማስቀረት የተደረገው ትግል የሥራውን ዓለም የአስተዳደር ዘይቤ ለመቀየር ያስቻለ ድል ማስመዝገቡም ይታወቃል፡፡

የዓለም ሠራተኞች አካልና የትግል አጋር የሆነው የአገራችን ሠራተኛም ከዓለም አቀፍ የላብ አደሮች የትግል ጉዞ የተለየ ታሪክ የለውም፡፡ በአገራችን ኢንዱስትሪ ማቆጥቆጥ ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ሠራተኞች መብታቸውን ለማስከበር ያደረጉት መራር ትግል በደማቅ ቀለም ተፅፏል፡፡ ትግሉ ሠራተኛው በሥራ ቦታ ክብርና ደህንነቱ፣ መብትና ጥቅሙ በተጠበቀበት ጥርጊያ መንገድ የሚጓዝበትን መደላድል መፍጠሩንም መላው የለውጥ ኃይሎች ያምናሉ፡፡

ስለሆነም ሜይዴይ ሲከበር ለትላንቶቹ ታጋይ ሠራተኞችና የሠራተኛ መሪዎች ክብርና ምስጋና ይድረሳቸው ማለት ይገባል፡፡ በዚሁ የትግልና የለውጥ መንገድ የቀጠሉት መላው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ዛሬ አገራችን ለደረሰችበት እድገት ምትክ የማይገኝለት የልማት ድርሻ ማበርከታቸውን ስንመለከት ኩራት ይሰማናል፡፡

የዘንድሮው ሜይዴይ የሚከበረው የኮሮና ቫይረስ በሚያስደነግጥ ፍጥነት ዓለምን በወረረበትና በመላው የሠው ልጅ ላይ አደጋ በደቀነበት ጊዜ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ዓለምም በምላሹ ኮቪድ 19ን የመከላከል ጦርነት አውጃ ፍልሚያ የገባችበት ቀውጢ ጊዜ በመሆኑ በየመስኩ የሚደረገው ትግል የተለያየ መስዋትነት እየጠየቀ ይገኛል፡፡ ወረርሽኙ በአንድ ፊት የሥራውን ዓለም ተጋላጭና ተጎጂ እያደረገ፣ በሌላ በኩል በዚያው ልክና ከዚያም በላይ ወረርሽኙ የሚመከትበት ጠንካራ ግንባር እያደረገው መቀጠሉ እሙን ነው፡፡

ከዚህ አኳያ የሥራው ዓለም ሠራዊት እራሱን እየጠበቀና ሌላውን እየታደገ በአሸናፊነት እንዲሻገር በተደራጀና በተቀናጀ አቅም አንድላይ መስራት ያለብን አሁን ነው፡፡ እዚሁ ላይ ሠራተኛውን በአሸናፊነት ይዞ መሻገር የሚለውን ቁልፍ ጉዳይ በቅጡ ልናጤነውና በጋራ ልናሰምርበት ይገባል፡፡ ዕውቅ የመከላከል መንገዶችንና የትንቃቄ ደረጃዎችን በመከተል ሠራተኛው ከወረርሽኝ እንዲጠበቅ ማስቻልና ዓለም ዓቀፍ አደጋውን ለመመከት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የሥራ ቦታ ለአገርና ለህዝብ ደህንነት የሚያበረክተውን ድርሻ በትጋት መወጣት ቀዳሚው ተግባር ነው፡፡

በሠራተኛው ላይ ከህግ አግባብ ውጭ ከሥራ የመናጠብና የሥራ ዋስትና እጦት እንዳይደርስ መጠበቅም ተባብሮና ተደጋግፎ የመሻገር ጉዟችን ቀዳሚ ትኩረት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ደህንነት መቆምንና በአንድነት መሰለፍን አብዝቶ ስለሚጠይቅ በዚሁ መስመር ላይ መገኘታችንን የምናረጋግጥበት ጊዜ ነው፡፡ ለዚሁ ስኬት ቀደም ሲል በመንግስት፣ በአሠሪና ሠራተኛ አካላት ምክክር የወጣው “የኮቪድ-19 የሥራ ቦታ ምላሽ የሦስትዮሽ ኘሮቶኮል” እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሥራ ቦታ ላይ የጣለውን ኃላፊነት እጅ ለእጅ ተያይዞ መተግበር ለስኬት ያበቃል፡፡

ይህ ችግር ማለፉ አይቀሬ ነው፡፡ መልካም ነገሮች ሁሉ በነበሩበትና ከነበሩበትም በላይ ከፍታ እየጨመሩ ይቀጥላሉ፡፡ ከዚህ አኳያ አለም አቀፍ ፈተናውን እንደአገር የምናልፍበት ብርታት የላቀ ዋጋ ያለው ከመሆኑም በላይ በታሪክ ደርዝ ይዞ የሚቀመጥ ስለሆነ ትጋታችን ሊጨምር ይገባል፡፡ በሥራው ዓለም ውስጥና ከዛም ባሻገር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመከላከል አገራዊ ጥሪ የቀረበው ለአስፈፃሚ አካላት፣ ለአሠሪና ሠራተኛ ስለሆነ የሰውን ልጅ የመታደግና ከወረርሽኝ ነፃ የሆነ የሥራ ቦታ የመፍጠር ጥረታችን ይቀጥል እላለሁ፡፡ በዚህ መንገድ ለመሻገር የሠራተኛና ማህበረዊ ጉዳይ ሴክተር የግንባርም፣ የደጀንም ተሰላፊ በመሆን ድርሻውን እንደሚወጣ ለማረጋገጥ እወዳለሁ ፡፡

ለመላው የኢትዮጵያ ሠራተኞችና ለሥራው ዓለም ተዋንያን መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ፡፡

አመሰግናለሁ !!

ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር

Report Page