ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

ለኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በሙሉ 
በያሉበት 

ጉዳዩ፡- የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ስርጭትን ለመግታት  የጋራ ስብሰባዎች ላይ ሊደረጉ የሚገቡ ጊዜያዊ ለውጦችን ይመለከታል

የጌታችንና የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን! 

በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) መስፋፋትን ለመግታት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህ ወረርሽኝ የሰው ልጆች ምን ያህል ውሱን እንደሆንን፣ ታላላቅ የተባሉ መንግሥታት ሳይቀሩ አቅማቸው በምን ሊፈተን እንደሚችል ያሳየ፣ ትልቅ የሆነ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ እና በእንዲህ አይነት ጭንቅ ዘመን መታመኛ የሚሆን እርሱ ብቻ እንደሆነ በግልጽ ያየንበት ነው፡፡ 

በእንዲህ አይነቱ ዓለምን ጭንቅ ውስጥ በከተተ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እኛ የምንታመነው ሁሉን በሚችልና ሁሉን ሊቆጣጠር በሚችል በእግዚአብሔር ስለሆነ ልንጨነቅም ሆነ ልንፈራ አይገባም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በመዝሙር 46፡1-2 ላይ “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም” ይላል፡፡ 

ይህም ሆኖ እያለ በዓለም ውስጥ እስካለን ድረስ ዓለም ውስጥ የሚሆነው ነገር ሁሉ የሚመለከተን እኛንም የሚነካን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህንን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት ለመከላከል የምንወስዳቸው እርምጃዎች የጥንቃቄና የበሽታውን መስፋፋትን ለመከላከል ያለሙ እርምጃዎች እንጂ የፍርሃት ወይም የእምነት መጉደል እርምጃዎች አይደሉም፡፡ ለራሳችንም ሆነ እድሜያቸው የገፋና በቀላሉ በበሽታው ሊጠቁ የሚችሉ ሰዎችን ጤንነት ለመጠበቅ ሲባል የምናደርጋቸው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንን ወረርሽኝ ለመግታት ለሕዝብ ጥንቃቄ ሲባል ብዙ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸውን ስብሰባዎች ለሁለት ሳምንት ያህል እንዳይደረጉ ማሳሰቢያ እንደሰጠ ይታወቃል፡፡ 

በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን የሚካሄዱ ብዙ ሰዎች በአንድ ላይ ተጠጋግተው የሚሰበሰቡባቸው እንደ እሁድ አምልኮ ጉባኤዎች፣ ኮንፍራንሶች፣ ሥልጠናዎችና ሌሎችም ተመሳሳይ ፕሮግራሞች ለሁለት ሳምንታት ያህል ማለትም ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እስከ መጋቢት 21 ድረስ እንዲቆሙ እናሳስባለን፡፡ 

የሰው ቁጥር ያልበዛባቸው ስብሰባዎችም ሲደረጉም ለቅድሚያ ጥንቃቄ በሕዝብ መገናኛ የተሰጡትን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ለምሳሌ በእጅ አለመጨባበጥ የመሳሰሉት እንዲከናወኑ እንመክራለን፡፡ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተቻለ መጠን የእጅ መታጠቢያ ቦታዎችና ሳሙናን ማዘጋጀት፣ በቤተ ክርስቲያን ያሉ ጤና ባለሙያዎች ለሕዝቡ ትምህርት እንዲሰጡ በማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ምሳሌ በመሆን እነዚህን መመሪያዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ እናሳስባለን፡፡ 

እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ በዚህ ጊዜ በጾምና በጸሎት ይህንን ወረርሽኝ እግዚአብሔር እንዲያስወግድልን የቤተ ክርስቲያናችን አማኞች ሁሉ በያሉበት ከመጋቢት 13-20 ቀን 2012 ዓ.ም በጾምና በጸሎት እንዲቆዩ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን መልዕክቷን ታስተላልፋለች፡፡ 

በቀጣይም በጉዳዩ ላይ በመጸለይ፣ ወረርሺኙን በሚመለከት የሚመጣውን ለውጥ በመከታተልና የሚሰጡ ተጨማሪ መግለጫዎችን በማየት ተጨማሪ ማሳሰቢያዎችን በየወቅቱ የምናስተላልፍ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

እግዚአብሔር በምህረቱ አገራችንና ምድራችንን ይጎብኝ!

Report Page