#ETH

#ETH


ነግ መንግሥትን አስጠነቀቀ!

በሰላም ከምንኖርበት ስፍራ እጅግ በሚያስደነግጥ ሁኔታ በታጠቀ ኃይል በአመራሮቻችን ላይ ወረራ ተፈጽሞብናል። በወቅቱ የመጣብን ኃይል ጥቂት ሲቪሎችን ለመያዝ የመጣ ሳይሆን አንድ ጦር ለመማረክ የመጣ ይመስል ነበር።»

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ «በሀገሪቱ ታሪክ እስከ ዛሬ ያልተፈጸመ» ያለው ግፍ እየተፈጸመብኝ ነው ሲል አማረረ። ኦነግ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ «የፖለቲካ ምህዳሩ የሰፋ መስሎን ወደ ሀገር ቤት ብንመለስም፣ መንግሥት በጦር ሠራዊቱ እና በሃብቱ (በከፍተኛ መዋዕለ ንዋዩ) በመተማመን በፓርቲያችን ላይ ግፍ እየፈጸመብን ነው» ብሏል። 

 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ዛሬ ለሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን በሰጠው በዚሁ መግለጫው በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰ በኋላ ሰላማዊ የትግል ስልት ውስጥ እያለ ይህንኑ ሂደት የሚያስተጓጉል እርምጃ በመንግሥት ኃይሎች እየተወሰደብኝ ነው በማለት መንግሥትን ከሷል። የኦነግ የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ሚካኤል ቦረን ባለፈው እሁድ በመኖሪያ ቤታቸው እያሉ ከሌሎች ስምንት አባላት ጋር በታጠቁ የመንግሥት ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉት አንድ እርሳቸው መሆናቸውን በመጥቀስ የመንግሥት የጸጥታ ኃይላት በወቅቱ ወረራ ፈጽመውብናል በማለት ተናግረዋል።

«በዚህ ሀገር ለውጥ መጥቷል በማለት ነበር ኦነግ ከመንግሥት ጋር በመስማማት በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ አላማውን ለማራመድ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰው። ነገር ግን በሰላም ከምንኖርበት ስፍራ እጅግ በሚያስደነግጥ ሁኔታ በታጠቀ ኃይል በአመራሮቻችን ላይ ወረራ ተፈጽሞብናል። በወቅቱ የመጣብን ኃይል ጥቂት ሲቪሎችን ለመያዝ የመጣ ሳይሆን አንድ ጦር ለመማረክ የመጣ ይመስል ነበር።»  አቶ ሚካኤል በማያያዝም አመራሮቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት አሁንም ድረስ ያልተመለሱላቸው ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስ ተወስደውብናል በማለት የመንግሥት ኃይሎቹን ከሰዋል። ድርጊቱም መንግሥት በሰላማዊ ምርጫ ሥልጣን እንዳይሸጋገር የወጠነው ሴራ ነው ይላሉ አቶ ሚካኤል።

«እኛ እንደምንጠረጥረው እና ይኼ ሁሉ ነገር እየኾነ ያለው ነጻ እና ፍትኃዊ ምርጫ እንዳካሄድ እና ህዝቡም መሪውን በሰላም መርጦ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዳይኖር በማሰብ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል የወጠነው ሴራ ነው። ጓዳችን አብዲ ረጋሳ የገባበትን ያጣነውም በዚሁ ምክንያት ነው ።»

ኦነግ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቢሮ ለመክፈት ሲንቀሳቀስ ቢሮ እንዳይከፍት በተኩስ ጭምር በማስፈራራት ከፍተኛ ጫና ሲደርስበት እንደቆየ በዚሁ መግለጫው አመልክቷል። ቢሮዎችን በከፈተባቸው ስፍራዎችም በርካታ አባላቱ መታሰራቸውን አስታውቋል። ከዚህ ባሻገር መሰል የኃይል ድርጊቶች እንዳይቀጥል የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ህዝቡ ርብርብ እንዲያደርጉ ኦነግ ጠይቋል። ካልሆነ ግን የማያባራ እሳት ሊቀጣጠል ይችላል ሲልም አስጠንቅቋል።

«አሁን መንግሥት እየፈጸመ ባለው ሁኔታ ነገሮች የሚቀጥሉ ከሆነ በዚህ ሀገር የማይጠፋ እሳት ማቀጣጠል እንደሆነ እናምናለን። በዚህች ሀገር እስከ ዛሬ ሆኖ የማያውቅ ነገር ሊሆን እየሄደ እንደኾነም እንገነዘባለን። መንግሥት በአስቸኳይ የማይስተካከል ከኾነ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን የማይወጡ ከኾነ፣ ሕዝቡ በፍጥነት ለመብቱ የማይታገል ከኾነ እና ይኼ ነገር መቆም አለበት ማለት ካልቻልን የማያባራ እሳት ያቀጣጠላል የሚል ስጋት አለን።»  ኦነግ በዛሬው መግለጫው እሁድ ዕለት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ከፍተኛ አመራሩ አቶ አብዲ ረጋሳ ዛሬም ድረስ የት እንዳሉ እንደማያውቅ አስታውቋል። ከዚህም ባሻገር ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፓርቲው የሚገኝበትን ችግር ተመልክተው ከጎኑ እንዲቆሙ በመጠየቅ መንግሥትም ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ስኬታማነት ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ጥሪ አቅርቧል።

[የጀርመን ድምፅ ሬድዮ]

Report Page