#ETH

#ETH


ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠ መግለጫ!

በዳኞቻችን ላይ ጥቃት በማድረስ ፍርድ ቤቶቻችን ተልዕኳቸቸውን ከመፈጸም አይገታቸውም!! የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ ተግተን እንሰራለን!!

በክልላችን የዳኝነት አገልግለሎት አሰጣጡ ፈጣን ፣ ፍትሃዊ ፣ ወጭ ቆጣቢ ፣ ተደራሽና እና ውጤታማ እንዲሆን ፣ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የክልላችን አስተማማኝ ሰላም እውን እንዲሆን እና ጤናማ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ የክልላችን ዳኞች ቀን ከሌሊት በቅንነት እና በታማኝነት በማገልገል ሙያዊ ግዴታቸውን እና ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

ዳኞቻችን ህዝብ እና መንግስት የሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ መከፈል ያለበትን ሁሉ ለመክፈል በመዘጋጀት የሐገራችን እና የክልላችን የጸጥታ ሁኔታ ስጋት ላይ ወድቆ በነበረበት ጊዜ ሳይቀር በፍርድ የሚያልቁ ጉዳዮች ላይ ያለማንም ተፅዕኖ በህግ ብቻ ውሳኔ በመስጠት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሰረታዊ ለውጥ በማምጣት የህዝብ ወገንተኝነታቸውን በተጨባጭ በማሳየት የዳኝነት አገልግሎቱ ላቅ እንዲል ታሪካዊ አሻራቸውን እያሳረፉ ያሉበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡

የሕግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ፣ ህዝቡ በመንግስት እና በዳኝነት አካሉ ላይ እምነት እንዲያጣ ፣ የዳኝነት አገልግሎቱ ምክንያታዊ እና ሚዛናዊ እንዳይሆን እና የፍትህ ስርዓቱን ለማዛባት በተለያዩ ወቅቶች በማዕከላዊ ጎንደር ፣ በሰሜን ጎንደር ፣ በደቡብ ጎንደር ፣ በአዊ ብሄረሰብ ፣ በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ በሚገኙ ዳኞቻችን ላይ የተለያዩ ጥቃቶች እና ተፅዕኖዎችን በመፍጠር የፍትህ ስርዓቱ በተለይም የዳኝነት አገልግሎቱ ከፍተኛ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ተደጋጋሚ ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም ዳኞቻችን ሁሉንም ተፅዕኖዎች በመቋቋም ፍትሃዊ የዳኝነት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ይህ የዳኞቻችን ጥንካሬ የማያስደስታቸው እና ዓላማቸው ህግ እና ስርዓትን ማፍረስ የሆኑ አካላት በፍርድ ቤት ተቋሞቻችን ላይ እና በዳኞቻችን ላይ በተለያዬ መገለጫ እያደረሱት ያሉት ያልተገባ ጥቃት እና ተፅዕኖ ቀጥሎ የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ/ም በደቡብ አቸፈር ወረዳ ዱር ቤቴ ከተማ በሚገኜው ወረዳ ፍርድ ቤት በሚሰሩ ሶስት ዳኞቻችን ላይ እጅግ አሳዛኝ እና አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ጥቃት አድርሰውባቸዋል ፤

የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፣ የባህር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የወረዳው ፍርድ ቤት የበላይ አመራሮችም በእነዚህ ሶስት ዳኞች ላይ ጥቃቱ ከተፈጸመ ጊዜ ጀምሮ ተጎጅዎችን በአካል አግኝቶ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመነጋገር ጉዳዩ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት የምርመራ ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችንን ሚና እየተወጣን እንገኛለን፡፡

ይህንን ህገ ወጥ ተግባር የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አጥብቆ ከማውገዝ ባለፈ እንዲህ ዓይነቱን ህግ እና ስርዓት የማፍረስ ተግባርን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ጥፋተኞች ለህግ እንዲቀርቡ እና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ ትግል የሚያደርግ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ህዝብ እንደ ህዝብ መንግስትም እንደ መንግስት በሰላማዊ ሁኔታ እንዲቀጥል ለማድረግ ጠንካራ እና ከስጋት ነጻ የዳኝነት አካል መኖሩ ግድ ይላል ፤ በዳኞቻችን ላይ እየተቃጣ እና እየደረሰ ያለው ህገ ወጥ ጥቃት እና ወከባም በግለሰብ ደረጃ በዳኞች ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በአጠቃላይ በመንግስት፣ በህዝብ እና በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጭምር የተፈጸመ ጥቃት ነው፡፡

ስለሆነም፡-

የተከበራችሁ በየደረጃው የምትገኙ ጉዳዩ የሚመለከታችሁ የመንግስት አካላት፡- በፍርድ ቤቶቻችንና ዳኞቻችን ላይ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃትና ወከባ በተመለከተ በማህበረሰቡ እና በአጠቃላይ ስርዓቱ ላይ የሚያስከትለውን አደጋ ከወዲሁ በመገንዘብ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በህዝብ እና በመንግስት የተጣለባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን ህዝቦች፡- ለህግ የበላይነት መረጋገጥ እና የገባነውን ቃል በተግባር ለማረጋገጥ እስከ ህይዎት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆነ የዳኝነት አካል ያለ መሆኑን በማመን መላው ህዝባችን ይህንን ድርጊት የፈጸሙ አካላትን አጋልጦ ለህግ በማቅረብ እና ለወደፊቱም መሰል ህገ ወጥ ተግባራት እንዳይፈጸሙ ለመከላከል ከጎናችን እንድትቆሙ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን ዳኞች፡- በዳኞቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ህገ ወጥ ተግባር እንዲቆም እና ደህንነቱ እና ነጻነቱ ተጠብቆ ኃላፊነቱን የሚወጣ የዳኝነት አካል እውን እንዲሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ ለወደፊቱ የምንሰራቸው በርካታ ስራዎች ያሉብን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ ሰዓት እየተፈጸመብን ያለው ጥቃት እና ወከባ በህዝብ የተጣለብንን ከፍተኛ አደራ እንዳንወጣ ወደ ኋላ ሊመልሰን የማይገባ፤ እንዲያውም ከመቸውም ጊዜ በላይ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ዘብ እንድንቆም እና ሙያዊ ግዴታችን እና ኃላፊነታችን ለመወጣት ጠንክረን እንድንሠራ የሚደርግ ነው፡፡

የተከበራችሁ የክልላችን ህዝቦች እና ዳኞች፡- በአጠቃላይ በዳኝነት አካሉ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ህገ ወጥ ተግባራትን ለማቆም በጋራ ሆነን የምንታገለው ሆኖ በአሁኑ ሰዓት በሶስቱ ዳኞቻችን የተፈጸመውን ህገ ወጥ ጥቃት በተመለከተ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ለጊዜው ቢሰወሩም በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ከፍተኛ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ መጠነ ሰፊ ክትልል በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

ስለሆነም የክልላችን ህዝቦችና ዳኞች ፡- ለተፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባራት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥቃት አድራሾችን ለህግ ለማቅረብ ያለሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመገንዘብ ውጤቱን በትዕግስት እንድትጠባበቁ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡

      የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት

      የካቲት 21/2012 ዓ/ም

          ባህር ዳር

Report Page