#ETH

#ETH


የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወካይ ከነእፓ እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያዩ!

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባዘጋጀው እና የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወካይ ወ/ሮ ሄተር ፈላይን በተገኙበት በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ እና ምርጫ 2012 አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል፡፡ አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል በተካሄደው እና ዓላማው በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፖለቲካ እና የምርጫ ዝግጅት ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መረጃ ለመሰብሰብ እንደሆነ በተገለጸው በዚሁ የውይይት መድረክ፣ የምርጫውን የግዜ ሰሌዳ፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በገዥው ፓርቲ መካከል ያለው ግንኙነት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያጋጥሟቸው ችግሮች፣ የምርጫ ቦርድ ዝግጅት እና አቅም፣ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል፡፡ 


በውይይቱ የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጠቃላይ የለውጥ ሂደቱን እና ምርጫ 2012 አስመልክቶ ያጋጠሟቸውን ችግሮች እንዲሁም ገዥው ፓርቲ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ በማድረስ ላይ ነው ያሏቸውን ልዩ ልዩ ጫናዎች ለኤምባሲው ተወካዮች ገልጸዋል፡፡ የመንግስት ሀብትን እና ሚዲያን በብቸኝነት መጠቀም ፓርቲዎቹ በገዠው ፓርቲ ላይ ካነሷቸው ችግሮች መካከል ይገኙበታል፡፡ የፓርቲዎቹ ተወካዮች የአሜሪካ መንግስት ከሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በእኩል ርቀት ላይ ሊቆም እና በተለይ ለገዢው ፓርቲ የተለየ ድጋፍ ማድረግ የፖለቲካ ሜዳውን እና በዚህ አመት በሚካሄደው ምርጫ ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ 


በስብሰባው ላይ የተገኙት የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንብር ዶ/ር አብዱልቃደር አደም ሽግግሩ የተሳካ እና ምርጫ 2012 ነጻ እና ፍትሀዊ ይሆን ዘንድ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በትብብር እና በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸው፣ የአሜሪካ መንግስትም ሆነ ሌሎች መንግስታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለሀገራችን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እና ለምርጫ 2012 ስኬታማነት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫዎቱ ጠይቀዋል፡፡ 


በውይይቱ ላይ የተገኙ ፓርቲዎች፡፡

1. ኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)

2. አማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን)

3. ኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

4. አረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉአላዊነት (አረና) 

5. ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)

6. የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንፍረንስ (ኦፌኮ)

7. ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)

Report Page