#TPLF

#TPLF


"ኢትዮጵያ በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች" - ህወሓት 

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጸሙ ከባድ ጥፋቶችና ቀውሶች ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ ጥፋትና መበታተን መንገድ በማምራት ላይ ትገኛለች ሲል ህወሓት አመለከተ። 

ድርጅቱ የተመሰረተበትን 45ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው "ተጀምሮ የነበረው ልማት ተስተጓጉሎ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል" ብሏል። 

ለዚህም ኢህአዲግ ሲመራበት የነበረውና "አንፀባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ የመጣው የልማታዊ ዲሞክራሲ መስመር ባለፉት 3 እና 4 ዓመታት በድርጅቱ ውስጥ ባጋጠመ የጥገኛ መበስበስ አደጋ" ምክንያት እንደሆነ ጠቅሷል:: 

ህወሓት በኢህአዴግ ውስጥ አጋጥሟል ያለውን "የመበስበስ አደጋ በፅናት በመታገል ዳግም ታድሶ ሥርዓቱን ለማዳን ከባድ ጥረት ቢያደርግም አባል ድርጅቶች ራሳቸውን ሳያጠሩ" በመቅረታቸው የድርጅቱ አመራር "ጥገኛ" ባለው ኃይል ስር ወድቋል ሲል ገልጿል። 

አመራሩም የልማታዊ ዲሞክራሲ መስመርን በመተው "ወደ ፍፁም ግለሰባዊ አምባገነናዊነት" መንገድ መግባቱንና በተሃድሶ ወቅት “መደገም የለባቸውም!” የተባሉ ጉድለቶችን "በከፋ ደረጃ በመፈፀም ላይ ይገኛል" ብሏል::

አክሎም ያለፉት 27 ዓመታት "ጠላቶች እንደሚሉት “የጨለማ ዘመን¡” ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች ከጭቆናና ከባርነት ቀንበር ተላቀው የሰላም፣ የልማትና ዲሞክራሲ ትሩፋትን የሚያጣጥሙበት የለውጥና የህዳሴ ዘመን ነበር" ብሏል።

መግለጫው በተጨማሪም "ሕገ መንግሥት ተጥሶ፣ የሕግ የበላይነት ተረግጦ፣ ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ እየተሸረሸረ፣ ተጠብቆ የነበረው ሰላም ደፍርሶ፣ የሕዝባችን አንድነት ተበትኖ፣ ልማት ተኮላሽቶ፣ የአገር ክብርና ሉዓላዊነት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ተደፍሮ አገራችን የውጪ ኃይሎች መፈንጫ ሆናለች" ሲል ይጠቅሳል::

ህወሓት እንደሚለው በዚህም ምክንያት "አገር ህልውና ከማንኛውም ጊዜ በከፋ ደረጃ አደጋ ላይ ወድቆ ይገኛል።"

የኢህአዴግ መፍረስን በተመለከተ "ፀረ- ዲሞክራሲ፣ በሕገወጥ አካሄድና በእህት ድርጅቶች ክህደት እንዲፈርስ ተደርጓል" በማለት የብልጽግና ፓርቲ መመስረትን ተከትሎም በፌደራልና በአዲስ አበባ አስተዳደር ያሉ የህወሓት አባላት ከሃላፊነት እንዲነሱ እየተደረገ ነው ብሏል። 

በአገሪቱ ውስጥም ፍፁም ፀረ-ዲሞክራሲና አፈና እንደንገሰ አመልክቶ "ፖለቲካዊ ምህዳሩ ጠቧል፣ የተለየ ሃሣብ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ጋዜጠኞች ይታሰራሉ፣ይታፈናሉ" ሲል ከሷል። 

ህወሓት በዚህ መግለጫው ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የፖለቲካ ኃይሎች መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን ለኤርትራ ሕዝብም ጥሪ አቅርቧል::

በዚህም "የትግራይ ሕዝብና ህወሓት በኤርትራ ህዝብ ጥያቄ ላይ ተደራድረውም ሆነ ተሳስተው አያውቁም" በማለት በጋራ በተከፈለ መስዋዕትነት የጋራ ድል መገኘቱን ጠቅሶ በዚህም "የራስህን ዕድል በራስህ የመወሰን መብት አረጋግጠሃል፤ በዚህም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ይኮራሉ" ብሏል:: 

አክሎም ባለፉት 20 ዓመታት አሰፈላጊ ባልሆነ ጦርነትና ግጭት ውስጥ መገባቱንና "ሁላችንም አስፈላጊ ያልሆነ ዋጋ ከፍለናል" በማለት በዚህም የፈጠረው ጠባሳ ቀላል እንደማይሆን ሁሉም የሚገነዘበው ሃቅ እንደሆነ አመልክቷል::

አስከትሎም "አሁን ግን የጋራ ጥቅማችንንና ታሪካዊ ዝምድናችንን በማደስ የጋራ እድገት ለማረጋጥ ወደሚያስችል ደረጃ እናሸጋግረው" ሲል ህወሓት ጥሪ አቅርቧል።

ህወሓት ይህንን መግለጫ ያወጣው የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 45 ዓመት በዓል ከጥቂት ቀናት በሗል የካቲት 11 ለማክበር ዝግጅት እያደረገ ባለበት ወቅት ነው::

[BBC]

Report Page