#ETH

#ETH


በወምበራ ወረዳ ኮንግ ቀበሌ በሰዎች ላይ የተፈፀመው ጥቃት፣ለፓለቲካ ፍጆታነት ሠበብ፣ ግጭት በማህበረሠቡ እንዲፈጠር በሚያደርጉና በተደራጀ ቡድን ሆን ተብሎ የተፈፀመ ሴራ መሆኑን የወምበራ ወረዳ መስተዳደር ጽ/ቤት ገለፀ።

ቡለን፣ ጥር 15/2012 ዓ/ም (ቡወመኮባቱ)

በመተከል ዞን በወምበራ ወረዳ ኮንግ ቀበሌ የተፈጠረው ግጭት፤ለፓለቲካ ፍጆታነት በሚንቀሳቀሱ ሰርጎ―ገቦች እንደተፈፀመ የወምበራ ወረዳ መስተዳድር ፅ/ቤት አስታውቋል።

የወምበራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሂካ አንበሳ በወረዳው ለሚገኙ የሚዲያ አካላት ጥር 14/2012 ዓ/ም በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት«የወምበራ ወረዳ ከዚህ በፊት አንፃራዊ ሠላም የነበረባት ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ግጭት እንዲፈጠርና የሠዎች ህይወት እንዲጠፋ በሚንቀሳቀቀሱ የተደራጁ ቡድኖች አማካኝነት ሠሞኑን በወረዳው የኮንግ ቀበሌ ጥቃት አድርሠዋል»ብለዋል።ዋና አስተዳዳሪው አክለውም«ጉህዴን የተባለው የፓለቲካ ድርጅት፤በቀበሌው በህገ― ወጥ መንገድ በመንቀሳቀስ፤ከገዢው የፓለቲካ ድርጅትና አባላት ጋር የሀሳብ ልዩነት በተደጋጋሚ እንዲፈጠር በማድረግ፤በሠዎች ላይ አሠቃቂ ግድያ፣ድብደባና ዝርፊያ ጥር 08/2012 ዓ/ም እንዲፈፀም መንስኤ ሆኗል ነው»ያሉት።ከዚህ በተጨማሪም በእለቱ በክልሉና ወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተደራጀው ቡድን ጥቃት ሊፈፅም እንደነበረም ዋና አስተዳዳሪው ጨምረው ገልፀዋል።

የወ/ወ/ፓሊስ ፅ/ቤት ኃላፊ ኮማንደር ማርዮ ቶለሳ በበኩላቸው«14 ሚሆኑ ሰዎች የደረሱበት እንዳልታወቀ፣ 8 ሰዎች እንደሞቱና የሁለት ሰዎች አስከሬን እስከ አሁን እንደተገኘ የገለፁ ሲሆን፣ ተጨማሪ የሟቾችን አስከሬን ለመሰግኘት የማጣራት ስራ እየተሠራ ነው» ብለዋል።እንደ ኮማንደር ማርዮ ተጨማሪ ገለፃ ከሆነ«ከጥቃቱ 33 የሚሆኑ የማህበረሠብ ክፍሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል፤በጥቃቱ ፍራቻና ስጋት ምክንያትም፤ሌሎች የጎረቤት ሙዝና፣በጎንዲ ቀበሌ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ለቀው ወደ ወረዳው መዲና የተሠደዱ ሲሆን፤ተመልሰው ሀብት ንብረታቸውን እንዲሰበስቡና ህዝቡን የማረጋጋት የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ» ተናግረዋል።

ከጥቃቱ ያመለጡ የኮንግ ቀበሌ ነዋሪዎችን ያነጋገርን ሲሆን« 9 ወገኖቻችን በጠራራ ፀሃይ አንገታቸው ተቀልቶ ሞተው አስከሬናቸው እስከ አሁን አልተነሳም፤የሀገር መከላከያ ሠራዊትም ፈጥኖ መድረስ ሲገባው ምንም እንኳ ጥቃቱ በደረሠበት ቦታ ዘግይቶ ቢደርስም ምንም ስራ አልሰራም፤ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ንፁሀን የአማራ ተወላጆች እስከ አሁን የደረሱበት አልታወቀም፤ከጥቃቱ የተረፉ ወገኖችም ለረሀብና በሽታ እየታደረግን ነው፤ድርጊቱን በፈፀሙ ግለሠቦችም ሆነ ቡድኖን ለይቶ የህግ ―የበላይነትን ከማስከበርና ተመጣጣኝ እርምጃ ከመውሰድ አንፃር የወረዳው አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለና ሌሎችንም አስተያየቶች ሠጥተዋል።

የወረዳው መንግስት በበኩሉ ግጭቱ በተፈጠረበት ቀበሌ የማረጋጋት ስራ አየተሠራ ነው፤ግጭት የፈጠሩ ግለሰቦችን የመለየትና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ በተቋቋመ መርማሪ ቡድን እየተጣራ መሆኑንና፤ነገር ግን የወረዳዋን ሠላም ወደ ቀድሞው ለመመለስ የሀገር ሽማግሌዎች፣የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም የወረዳው ህዝብ ከመንግስት ጎን መሠለፍ እንደሚገባው ጥሪ አቅርቧል።

[የወንበራ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን]

Report Page