ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

የጥምቀት በዓል ለቱሪዝም እድገት ያለው ፋይዳ በሚል ርዕስ ውይይት ተካሄደ

አክሱም ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የጥምቀት በዓል ታሪካዊ አመጣጥ ለቱሪዝም እድገት ያለው ፋይዳ በሚል ርዕስ ተካሄደ፡፡

በወይይቱ የታሪክ ተመራማሪ ፣ ፀሃፊና ደራሲ መምህር ገብረኪዳን ደስታ ስለ ጥምቀት ታሪካዊ ዳራ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን የጥምቀት በዓል አከባበር መሰረቱ በኣክሱም ከተማ መሆኑን በመግለፅ ነገር ግን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በዓሉን በስፋት ለማክበር እየተሰራ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡ የጥምቀት በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ከዘመን ዘመን ከትውልድ ትውልድ እየተከበረ መምጣቱን በመግለፅ በዓሉ ይበልጥ ለጎብኚዎች ለማስተዋወቅ መሰራት እንዳለበት አክለው ገልፀዋል፡፡ 

በተጨማሪ መምህር ገብረኪዳን አክሱም የማህሌታይ ቅዱስ ያሬድ እና ግእዝ ቋንቋ መገኛ ከተማ መሆንዋን በመግለፅ በኣክሱም ፅዮን ቤቴክርስትያን የሚገኘው የቅዱስ ያሬድ የአብነት ትምህርት ቤት ወደ ኮሌጅ ደረጃ ማደግ እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ ይህ የቅኔ ፣ የመፅሃፍ እና የማህሌት ትምህርቶች የሚሰጥበት የአብነት ትምህርት ቤት በኮሌጅ ደረጃ እንዲያድግ ለማድረግ ባለሃብቶች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ሊሰራ እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን ለግሰዋል፡፡ 

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዘኛ እና የግዕዝ ቋንቃዎች መምህር ፍስሃ ሃይሉ በበኩላቸው ስለ ኣክሱም ዘመነ መንግስት ፣ ስለ ኣክሱም ከተማ ስያሜ እንዲሁም ስለ ጥምቀት ታሪካዊ አመጣጥ ለተሳታፊዎች ገለፃ አድርገዋል፡፡  የጥምቀት በዓል የክርስትና እምነት በንጉሰ ነገስት ኢዛና ዘመን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ መከበር እንደተጀመረ በመግለፅ በሃፀይ ገብረመስቀል ዘመን ደግሞ በዓሉ ውሃ በሚገኝበት ቦታ ታቦት ይዞ በመሄድ ይከበር እንደነበር መምህር ፍስሃ ሃይሉ አክለው ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ያሬድ የጥምቀት በዓልን በማስመልከት የተለያዩ ድርሰቶች መድረሱን ገልፀዋል፡፡ 

በቅርቡ በዮኔስኮ በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱ ሳይለቅ ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ አስተዋፅኦ እንዲኖረው መደረግ እንዳለበት በውይይቱ ተገልጿል፡፡ እንዲሁም ሕብረተሰቡን በማሳተፍ በዓሉ በየዓመቱ በድመቀት በማክበር ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ በውይይቱ ተገልጿል፡፡ 

በዚህ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የተካሄደው ወይይት ላይ ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ የታደሙ ሙሁራን፣ ከአክሱም ፅዮን ቤቴክርስትያን የታደሙ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ሰዎች ተገኝተው የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች በማቅረብ ተሳትፈዋል፡፡

Report Page