#ETH

#ETH


በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከከምባታ ጠምባሮ ዞን አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ!!

"ልማትን ከሠላም ነጥሎ ማየት አይቻልም!!"

የዞናችን ሕዝቦች ሰላምን አብዝተው የሚፈልጉ እና ለተግባራዊነቱም በንቃት የሚንቀሳቀሱ ናቸው። የከምባታ ጠምባሮ ዞን ሠላማቸውን ለማስጠበቅ ከሚከፍሉት ዋጋ ባልተናነሰ መልኩ ለልማት ቅድሚያ የሚሰጡ እና ልማትንም በተግባር የሚሠሩ ሕዝቦች ያሉበት ዞን ነው። 

ለዚህ ምስክር የሚሆነው ባለፉት ዓመታት የሕዝቡን ሰላም የሚያደፈርሱ የልማት፥ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ውጫዊ ጫናዎች ቢኖሩም ሕዝቡ የሰላምን ዋጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ለሠላም ዘብ መቆሙ ነው። ጉዳዮ በቀጥታ የሚመለከተው መንግሥትም ችግሮቹን ለመቅረፍ በየደረጃ እና አቅም በፈቀደ መጠን የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።

በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የመልማት ፍላጎት ቢኖርም ፍላጎቶቹን ለማሟላት በመንግስት በኩል በተደጋጋሚ በሚስተዋለው የሀብት አቅም ውሱንነት እና ኢ - ፍትሃዊነት የተነሳ በርካታ ያልተመለሱ የሕዝብ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸው ከማናችንም የተሰወረ አይደለም።

እነዚህ የልማት ጥያቄዎች በተለይም ከመንገድ፥ ከውሃ፥ ከኃይል አቅርቦት እና ከሥራ አጥነት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን የሚፈቱ የኢንዱስትሪ ፓርክ፥ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሚጠቅም የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጫ በሚሆን መልኩ የዱራሜ ካምፓስን ወደ ዩኒቨርስቲ ማሳደግ እና ወዘተ የዞናችን ሕዝቦች የረጅም ጊዜ ቅሬታዎች እና ጥያቄዎች መሆናቸው ይታወቃል።

የዞናችንን ሕዝቦች ጽኑ የሆነ የመልማት ፍላጎትን ተከትለው የሚያነሷቸው ትክክለኛ የልማት ጥያቄዎችን በየደረጃ ያለው አመራር ከእርሱ የሚጠበቀውን ድርሻ እየተወጣ እና በሚፈጠሩ መድረኮች ሁሉ በተደራጀ እና ባልተደራጀ መልኩ የክልልም ይሁን የፌዴራል መንግስት ምላሽ እንዲሰጥ ትግል እያደረገ ይገኛል። በዚህም ብቻ ሳይወሰን በዞን እና በወረዳ አስተዳደር አቅም የሚሠሩ ልማቶችን ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እና በማስተባበር እየሠራ ይገኛል።

የፌዴራል እና የክልል መንግሥታትም ለተጠየቁ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ሂደት ላይ ይገኛሉ። ከተጠየቁ ጥያቄዎች ውስጥ የሀላባ - ዳምቦያ - አንጋጫ - አመቾ ዋቶ እና የዱርጊ - ወልደሃኔ ድልድይ እና መንገድ ጥያቄዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆን የሁለቱም መንገድ ፕሮጀክቶች ሥራ በያዝነው ዓመት እንዲጀምር በጀቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በኩል ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ ስለመሆኑ ተገልጿል።

እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ መንገዱ ወደ ሌላ አካባቢ ተቀይሯል በሚል አሉባልታ በሕዝብ ውስጥ ትልቅ ቁጣ እንዲቀሰቀስ ተደርጓል። በሌላ በኩል ከሀላባ - ዳምቦያ - አንጋጫ - አመቾ ዋቶ ያለው መንገድ ጊዜያዊ ችግሩን ለመፍታት ወቅታዊ ጥገና የሚያስፈልገው በመሆኑ የደቡብ መንገዶች ባለስልጣን የዱራሜ ዲስትሪክት የመንገዱን ጥገና ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል። 

የትኛውንም ጥያቄ ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረው ሰላማዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ በሰለጠነ መልኩ ማቅረብ ሲቻል በሕዝቡ በራሱ ተሳትፎ እና ባለው ውስን ሀብት የተሠሩ ማኅበረሰቡ በየዕለቱ የሚገለገልባቸውን አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ማፍረስ፥ መሰባበር እና ተገቢውን አገልግሎቶች እንዳይሰጡ ማስተጓጎል ከባህላችን እና ከምንታወቅበት እሴት ያፈነገጠም ጭምር ነው።

ስለሆነም መላው የዞናችን ኅብረተሰብ ሰላሙን ለማስጠበቅ እና የሚሠሩ የልማት ተግባራት ለአፍታም ሳይስተጓጎሉ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ድርሻውን እንዲወጣ እየጠየቅን የልማት ጥያቄዎችን እንደሽፋን በመጠቀም የተሳሳተ መረጃ ለሕዝባችን በማቃበል የሕዝባችንን ሰላም የሚያናጉ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳለን።

በመጨረሻም ከሰሞኑ የተከሰተውን ሁከት እና ብጥብጥ በማረጋጋት አካባቢው ወደ ነበረበት ሰላም እንዲመለስ ላደረጉ መላው ሕዝባችን ያለንን ልባዊ አድናቆት እና ምስጋና እናቀርባለን።

እግዚአብሔር ዞናችንን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!!

           የከምባታ ጠምባሮ ዞን አስተዳደር

            ጥር 11 ቀን 2012 ዓ/ም

                 ዱራሜ

Report Page