ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

በዓለማችን የመጀመሪያ የሆኑ ሕይወት ያላቸው ሮቦቶች ተሠሩ 

“ሮቦቶቹ በሰው አካል ውስጥ መድኃኒት ለመሸከም እና የደም ቧንቧዎች ውስጥ በመጓዝ የረጋ ደምን የማፅዳት ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ” - ጥናቱ 

የአሜሪካ ሳይንቲስቶች በዓለማችን የመጀመሪያ የሆኑ ሕይወት ያለቸው እና ራሳቸውን መልሰው መጠገን የሚችሉ ሮቦቶችን ከእንቁራሪት ግንደ ሕዋሳት /stem cells/ መሥራት መቻላቸውን ተናገሩ። 

'ዜኖፐስ ሌኒስ' ከተባሉ የአፍሪካ እንቁራሪቶች ዝርያ በተወሰዱ ግንደ ሕዋሳት የተሠሩት ሮቦቶቹ፣ 'ዜኖቦትስ' የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። 

እነዚህ ሮቦቶች /ማሽኖች/ ከአንድ ሚሊሜትር ያነሰ (0.04 ኢንች) የሆነ ስፋት ያላቸው ሲሆን ይህ አነስተኛ መጠናቸው በሰው ሰውነት ውስጥ መንቀሳቀስ ያስችላቸዋል ተብሏል። 

ሮቦቶቹ መራመድ እና መዋኘት እንዲሁም ያለምግብ ለሳምንታት መቆየት የሚችሉ እና በቡድን የሚሠሩ መሆናቸውም ነው የተነገረው። 

ከተፍትስ ዩኒቨርሲቲ የአለን የግኝት ማዕከል ጋር በመሆን የሮቦቶቹን ምርምር ያከናወነው ቬርሞንት ዩኒቨርሲቲ፣ "ማሽኖቹ ሙሉ ለሙሉ አዲስ የሕይወት ቅርፅ ናቸው" ሲል ገልጿቸዋል። 

ግንደ ሕዋሳት ተለይተው የማይታወቁ እና ወደ ሌሎች የሕዋስ ዓይነቶች (ለምሳሌ የደም ሕዋስ) ወደ መሳሰሉት መቀየር የሚችሉ ሕዋሳት ናቸው። 

ሮቦቶቹን የሠሩት ጥናት አድራጊዎች ግንደ ሕዋሳትን ከእንቁራሪት ሽሎች በመውሰድ እና እንዲፈለፈሉ በማድረግ ካሳደጉ በኋላ በረቀቀ ኮምፒውተር ዲዛይን ወደ ተደረጉ የተለያዩ የሰውነት ቅርፆች እንደለወጧቸው ነው የተነገረው። 

የቬርሞንት ዩኒቨርሲቲ በዚህ ላይ ባወጣው የፕሬስ መግለጫው፣ "እነዚህ ቅርፆች በተፈጥሮ ውስጥ ታይተው የማይታወቁ" ናቸው ብሏል። 

ከምርምር አድራጊዎቹ አንዱ የሆኑት የቬርሞንት ዩኒቨርሲቲው ጆሹዋ ቦንጋርድ፣ ማሽኖቹ ለየት ያሉ አዲስ ግኝቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። 

"[ማሽኖቹ] ከቀድሞዎቹ ሮቦቶች ጋር የማይመሳሰሉ፣ ከእንስሳት ዝርያ ጋርም የማይገናኙ ናቸው፤" ያሉት ተመራማሪው "ሕይወት ያለው እና ፕሮግራም ሊደረግ (በኮምፕዩተር ክትትል ሊደረግለት)  የሚችል አዲስ ዓይነት ሥሪት" መሆኑን ነው የገለጹት። 

ዜኖቦትስ እንደ ቀድሞዎቹ ሮቦቶች የሚያብረቀርቁ ዘንጎች ወይም የሮቦት እጆች የላቸውም፤ ይልቁንም ቅርፅ አልባ የሆነ ትንሽዬ ተንቀሳቃሽ ሥጋ የሚመስሉ ናቸው። 

ይህ ደግሞ ሌሎች ብረት ለበስ የሆኑ ወይም ከፕላስቲክ የተሠሩ ሮቦቶች መሥራት የማይችሉትን ሥራ ማከናወን እንዲችሉ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል። 

ዜኖቦትስ ባዮሎጂካል ማሽኖች በመሆናቸው ለአካባቢ ተስማሚ እና ለሰው ልጆች ጤናም ምቹ መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል። 

እነዚህ ማሽኖች ዘርፈ-ብዙ አገልግሎቶች ሊሰጡ እንደሚችሉም ነው ጥናቱ የጠቆመው፡፡

ከእነዚህም መካከል በሬዲዮአክቲቭ የሚፈጠር ቆሻሻን ለማፅዳት፣ በውቅያኖሶች ውስጥ ያሉ ጥቃቅን ፕላስቲኮችን ለመሰብሰብ፣ በሰው አካል ውስጥ መድኃኒት ለመሸከም እና የደም ቧንቧዎች ውስጥ በመጓዝ የረጋ ደምን የማፅዳት ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ ተብሏል። 

ዜኖቦትስ ለቀናት ወይም ለሳምንታት ተጨማሪ ንጥረ ነገሮችን ሳያገኙ በቀዝቃዛ አካባቢዎች ውስጥ መኖር የሚችሉ መሆናቸው በሰውነት ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት ለማድረስ ተስማሚ ያደርጓቸዋል። 

ከእነዚህም ፈጣን ተግባሮች ባሻገርም ዜኖቦትስ ተመራማሪዎች ስለ ሕዋስ ባዮሎጂ ብዙ እንዲማሩ ሊረዱ ይችላሉ ተብሏል። ይህም ለሰው ልጆች ጤና እና ረጅም ዕድሜ የመኖር መፃኢ ለውጦች በር ከፋች ይሆናል ተብሏል። 

( EBC ~ሲኤንኤን )

Report Page