ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በተወሰዱ እርምጃዎች ተጨማሪ ማብራሪያዎች

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተከስቶ በነበረው የሰላማዊ መማር ማስተማር እጦት በተለያዩ ደረጃዎች አሉታዊ አስተዋፅኦ አድርገዋል በተባሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና የጤና ባለሙያ ላይ የዩኒቨርሲው ሴኔት፣ የፌደራል ልዑካንና የተለያዩ የፀጥታ አካላት በተገኙበት ከቀላል የዲሲፕሊን እርምጃ እስከ ስንብት የደረሰ ቅጣት መወሰዱና ማሳወቃችን ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ ያገኘነው ግብረ-መልስ አበረታች ቢሆንም እርምጃውን በዝርዝር ያልተረዱ አስተያየት ሰጭዎች እንዳሉ በመገንዘባችን ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት አስፈልጓል፡፡

እርምጃ የተወሰደባቸው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ክፍሎች፡-

* ተደጋጋሚ ምክር እና ተግሳጽ ተሰጥቷቸው ሊማሩ ያልቻሉ፣

* ከበርካታ ተጠርጣሪዎች መካከል በማስረጃ ተለይተው የወጡ፣

* በዩኒቨርሲቲው የፀጥታ ሰዎች፣ በክልሉ አድማ ብተና፣ ኮማንድ ፖስትና በፌደራል ፖሊስ አማካኝነት ጥፋት ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ የተያዙ፣ 

* ከተለያዩ ስውር ቦታዎች በተገጠሙ የደህንነት ካሜራዎች የተያዙ ይገኙበታል፡፡

የጥፋቱ ዓይነትም፡- 

* ተማሪዎችን ለዓመጽ በማነሳሳት እና ሁከት በመፍጠር፣

* ተማሪዎች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ በማድረስ (በአካል፣ በስልክ፣ በፅሑፍ መልዕክት በመጠቀም)፣ 

* ግቢ ውስጥ ጩቤ ይዞ እጅ ከፍንጅ በመያዝ፣ 

* ብሔር ተኮር ጥቃት፣ የአካልና የስነ-ልቦና ጉዳት በማድረስ፣

* ግጭት ቀስቃሽ ፅሑፎችን ሲበትኑ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው፣ 

* ግርግሩን በመጠቀም ሞባይል ሰርቀው በደህንነት ካሜራው እገዛና  እጅ ከፍንጅ የተያዙ፣

* የሁለት ግቢዎች መታዎቂያ ይዞ በመገኘት (አንደኛው ፎርጅድ የሆነ)፣ 

* ቤተ-መፅሐፍትና ምግብ ቤት ላይ እርችት በመተኮስ ሁከት ሲፈጥሩ እጅ ከእጅ የተያዙ፣ 

* አቀጣጣይ (ላይተር) ቁሶችን ይዘው ሲገቡ የታያዙ፣ 

* ጫትና አሽሽ ይዘው የተያዙ፣ 

* ክፍል ውስጥ ባልተገኙ መምህራን የተወሰደ ቅጣት 

* አንድ መምህር በግርግሩ ወቅት ከ140 በላይ ተማሪዎችን ከግቢ ውጭ አንድ አዳራሽ ውስጥ በመቆለፍ በደላላ በሌሊት ሊሸኝ ሲል የተያዘና ከታፈኑት ተማሪዎች መካከል አንዷ ሴት ተማሪ ታፍና ልትሞት ስትል መረጃው ሲደርሰን ክሊኒክ እንድትደርስ በማድረግ ህይዎቷ እንዲተርፍ ተደርጓል፣

* አመፁን ከሚያባብሱ ተማሪዎች ጀርባ ሆነው ዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራውን እንዳይሰራ ሲያደርጉ የነበሩ መምህራን፣ 

* አመፅ ቀስቃሽ ፅሑፎችን ሲፅፉ የነበሩ እና ስራ ገበታቸው ላይያልተገኙ  መምህራን፣ 

* በሁለት ተቋማት ላይ በቋሚነት ተቀጥሮ  ሲሰራ የነበረና ኃላፊነቱን ያልተወጣ ፕሮክተር፣ 

* በፍተሻ ወቅት የአልኮል ጠርሙሶች የተገኘበት ፕሮክተር 

* በቃጠሎው ወቅት የተማሪ ህይወት ሲያልፍ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ፕሮክተሮችና የአንቡላስ ሹፌሮች፣ 

*  ተቋሙ ሳያውቀው የጤና ባለሙያዎችን ስራ አስቁሞ በመሰብሰብ ዓመፅ በማነሳሳትና የመንግስት የስራ ስዓትን በማባካን፣

* አሉባልታ በመንዛትና ግጭት በመፍጠር የተጠረጠረን ተማሪ ለህግ እንዳይቀርብ በመደበቅ የተደረሰበት በዋናነት የሚጠቀሱ ጥፋቶች ናቸው፡፡ 

ስለሆነም እርምጃዎቹ ጥፋትን እንጅ ብሔርን መሰረት ያላደረጉ እንደየ ጥፋታቸው አይነት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተለያዩ የስነ-ምግባር ደንቦች የተወሰደ መሆኑን እንገልፃለን፡፡ በቀጣይም በተመሳሳይ ጥፋት በሚሳተፉ አካላት ላይ አስተማሪና ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ የአብዛኛውን ትምህርት ፈላጊ ተማሪዎቻችን መብት የምናስጠብቅና የተቋማችን ህግጋት የምናስከብር መሆኑን እንገልፃለን፡:

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

Report Page