#ETH

#ETH



የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት/መኢአድ/በፖለቲካዊ መስመሩን እና ወቅታዊ የሀገሪቱን ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ከአባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ዛሬ በባህርዳር ከተማ ውይይት አካሄደ።

የድርጅቱ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት መኢአድ ላለፉት 28 ዓመታት ታግሏል።

ድርጅቱ ባካሄደው ትግል የህብረተሰቡ የንቃተ ህሊና እያደገ በሀገሪቱ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ እንዲመጣ የድርሻውን መወጣቱን ተናግረዋል።

ለውጥ መጣ ተብሎ ህዝቡ ገና መረጋጋት ሳይጀምር የተከተለው የፖለቲካ ውጥረት ሀገሪቱን ፈተና ውስጥ ማስገባቱን ገልጸው አባላቱና ህዝቡ ማወቅና እራሳቸውን መዘጋጀት ያለባቸው ቀደም ሲል ከነበረው ትግል የበለጠ ማጠናከር እንደሆነ ጠቁመዋል።

አቶ ማሙሸት እንዳመለከቱት እንደ ድርጅታቸው አቋም ወደ ምርጫ ከመገባቱ በፊት አስቀድሞ ውይይት፣ ድርድርና ክርክር ብሎም ሀገራዊ መግባባት መደረስ ይኖርበታል።

መምህር ታዬ ቦጋለ በበኩላቸው አሁን ላይ የሀገር አንድነት፣ የህዝቦች መፈቃቀርና መዋደድ፣ በጋራ የመበልጸግና በፍትሃዊነት የመጠቀም ፍላጎት የሌላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች እየተበራከቱ ለሀገሪቱ አሳሳቢ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ህዝቡ ከውጭና ከውስጥ ከፋፋይ ኃይሎች ሴራ ሳይጠለፍ አንድነቱን አጠናክሮ ለሀገር ህልውና እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከልም አቶ ደምሳሽ አየሁ እንዳሉት አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት መኢአድ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ውህደት ፈጥሮ የድርሻውን መወጣት አለበት።

ውህደት መፍጠር ካልተቻለ የህዝቡ ድምጽ ስለሚከፋፈል የማሸነፍ እድሉ ስለሚመነምን በዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ ከአማራ ክልል ዞኖች የመጡ የድርጅቱ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ተሳትፈዋል።

(ENA)

Report Page