#ETH

#ETH


የኢትዮጵያ ስርዓተ-ትምህርት ሊቀየር ነው!

በኢትዮጵያ ሥራ ላይ ያለው ስርዓተ-ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ሊቀየር መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። አዲሱን ስርዓተ-ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የስድስት ዓመታት ጊዜን እንደሚጠይቅም ተመልክቷል።

ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አሁን በስራ ላይ ያለው ስርዓተ-ትምህርት ያሉበትን ችግሮችና ጠንካራ ጎኖች ለመለየት የሚያስችል አንድ ዓመት የወሰደ ጥናት ተካሂዷል። በዚህ ጥናት መሰረትም የአገሪቱ ስርዓተ-ትምህርት በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉበት እንደሆነ መረጋገጡን ጠቅሷል።

በሥራ ላይ ያለው ስርዓተ ትምህርት ህጻናት በእድሜያቸውና በክፍላቸው ደረጃ ማወቅ የሚጠበቅባቸውን እውቀትና ክህሎት እያስጨበጠ አለመሆኑ ከችግሮቹ መካከል እንደሚጠቀስ በሚኒስቴሩ የስርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው ተናግረዋል።

ስርዓተ ትምህርቱ በይዘት የታጨቀና ለሙያ ነክ ትምህርቶች ተገቢውን ትኩረት ያልሰጠ መሆኑም ከድክመቶቹ መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ አጠቃለይ የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት ለመቀየርና ለማሻሻል የአስር ዓመት ፍኖተ ካርታ መቀየሱን ጠቅሰው ስርዓተ-ትምህርቱን ብቻ በሚመለከት የሶስት ዓመት ልዩ እቅድ ተዘጋጅቶ በ2011 ዓም ወደ ስራ መገባቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በዚህም የመጀመሪያ ስራ የስርዓተ ትምህርት ማዕቀፉን ማዘጋጀት እንደሆነ ያነሱት ዳይሬክተሩ በዝግጅቱም ሁሉም ክልሎች በባለሙያ እንዲወከሉ መደረጉን አመልክተዋል። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃን ጨምሮ በሁሉም የትምህርት እርከኖች የተወከሉ መምህራንና ባለሙያዎች በዝግጅት ሂደቱ እንዲሳተፉ መደረጉንም ተናግረዋል።

ማዕቀፉ በባለሙያ ከተሰራ በኋላ የተለያዩ ደረጃዎችን የሚያልፍ ሲሆን፣ በአገሪቷ የሚገኙ ትልልቅ ተቋማትን የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሙያ ማህበራትንና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ለውይይት ክፍት ተደርጎ ግብዓት ከተወሰደ በኋላ ይጸድቃል ነው የተባለው። የስርዓተ ትምህርቱ ማዕቀፍ ከተዘጋጀ በኋላ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ የትምህርት ዓይነቶች ይዘት እንደሚቀየር ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አስፋው አብራርተዋል።

በ2013 ዓ.ም መጀመሪያ አዲሱ ስርዓተ-ትምህርት በመላው አገሪቷ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ይደረጋል። አዲሱን ስርዓተ-ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የስድስት ዓመታት ጊዜን እንደሚጠይቅም ተመልክቷል።

(ኢዜአ)

@tikvahethiopia @tikvahethioiaBot

Report Page