#ET

#ET


ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በማንኛውም የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ በአዲስ አበባ የሚሰጠው ስልጠናዎች እውቅና ፈቃድ ያልተሰጠው መሆኑን ኤጀንሲው ገለጸ፦

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በቁጥር 01/መ-4/631/07 የካቲት 19 ቀን 2007 ዓ.ም ከየካቲት 2007 ዓ.ም እስከ ጥር 2010 ዓ.ም ድረስ በኢኮኖሚክስ ፣በማኔጅመንት ፣በአካውንቲንግ ኤንድ ፋይናንስ ፣በቢዝነስ ማኔጅመንት ፣ሲቪክስ ኤንድ ኢቲካል ኢዱኬሽን ፣ኢንግሊሽ ኤንድ ሊትሬቸር ፣ጂኦግራፊ ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ስተዲስ ፣ሂሳብ ፣ኢትዮጵያን ላንጉጅ ኤንድ ሊትሬቸር ፣ላንድ አድሚኒስትሬሽና የህግ ስልጠና መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ እንዲያስተምር የዕውቅና ፈቃድ ተሰጥቶት ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የትምህርት ሚኒስቴር በ28/12/07 በቁጥር ጠ-259/6384/07 ባስተላለፈው ሰርኩላር አማካይነት ኤጀንሲው ጳጉሜ 4 ቀን 2007 ዓ.ም በቁጥር 01/መ/4/4671/07 ለዩኒቨርሲቲው በጻፈው ደብዳቤ በአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ማዕከሉ ከላይ በተጠቀሱት የትምህርት ፕሮግራሞች ለተቋሙ ተሰጥቶት የነበረውን የእውቅና ፈቃድ በመሻር ተቋሙ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ማስተባበሪያው የተቀበላቸውን ተማሪዎች ብቻ እንዲያስጨርስና የአዲስ ተማሪዎች ቅበላ እንዳያካሄድ እና ስልጠናውን እንዲያቆም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ነገር ግን ዩኒቨርስቲው ኤጀንሲው በሰጠው የእውቅና ፈቃድ መሰረት ከየካቲት 2007 አስከ ጳጉሜ 2007 ዓ.ም ድረስ ተቀብሎ የመዘገባቸውን ተማሪዎች ብቻ ማስጨረስ ሲገባው ህግንና መመሪያን በመተላለፍ ተማሪ ተቀብሎ እያስተማረ ስለመሆኑ በተጨባጭ አረጋግጠናል፡፡

እንዲሁም ሰኔ 27 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር ከ/ት/ሚ/ር/108/2017/11 የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለሁሉም የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማ ባስተላለፈው ሰርኩላር ዩኒቨርስቲዎች ከእንደዚህ ዓይነት ድርጊት እንዲቆጠቡ ቢያስጠንቅቅም ዩኒቨርሲቲው አሁንም በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ ዳግማዊ ሚኒሊክ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የርቀትና ተከታታይ ትም/ፕሮ/ማስ/ጽ/ቤት በሚል በተከራየው ቢሮዎች ውስጥ በህግ መሰረት ፈቃድ ሳይሰጠው በከፍተኛ ትምህርት መስክ በአዲስ አበባ በርቀትና በቅዳሜና እሁድ የትምህርት መርሃ ግብሮች በመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ተቀብሎ በመመዝገብና በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ኤጀንሲው ባደረገው ማጣራት ያረጋገጠ በመሆኑ ተማሪዎችም ሆኑ የተማሪ ወላጆች ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ትምህርት መስክ በአዲስ አበባ ከተማ በርቀት የትምህርት መርሃ ግብሮች ተማሪ ተቀብሎ እንዲያስተምር ከኤጀንሲው የእውቅና ፈቃድ ያልተሰጠው በመሆኑ የተማሪ ምዝገባ ማከናወን ስለማይችል ህብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ እያሳሰብን ኤጀንሲው ወደፊት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመመካከር ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ለህብረተሰቡ ያስገነዝባል፡፡

በመጨረሻም በመማር ላይ የነበሩ ተማሪዎችን በተመለከተ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር በመሆን መፍትሔ የሚሰጣቸው በመሆኑ ምንም ዓይነት ሃሳብ ውስጥ እንዳይገቡ እያሳስብን ነገር ግን ለ2012 የትምህርት ዘመን የተመዘገቡ አዲስ ተማሪዎች ህጋዊ እንደማይሆኑ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ

ነሐሴ 21 ቀን 2011 ዓ.ም.

@tikvahethiopia @tikvahethiopia

Report Page